December 17, 2013
ታህሳስ 7 2006 ዓም የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ከተመሰረተ አንድ አመት ሞላው። አንድ አመት በጭንቅና በአሳር ለተያዘች የዛሬይቱ ኢትዮጵያና ህዝቧ እጅግ ረጅም ግዜ እንደሆነ ህዝባዊ ሃይሉ በሚገባ ይገነዘባል። ባላፈው አንድ አመት ውስጥ የኢትዮጵያን ህዝብ የመከራ የአሳርና የውርደት ህይወት ይበልጥ እየሰፋ፣ የሚፈጸምበት ግፍ ይበልጥ እየገዘፈ መሄዱን አይተነዋል። በሃገርና በህዝብ ላይ እየወረደ ያለውን ወያኔ ወለድ የስቃይና የፍዳ ናዳ በቅጡ ላጤነው ሃገሪቱና ህዝቧ የአዳዲስ የስቆቃና የመከራ አይነቶች መፈተኛ ቤተ ሙከራዎች እየተደረጉ ለመሆኑ ጥርጥር አይኖረውም። ለሚራበው ለሚረገጠው በግፍ ለታጎረው፣ በኑሮ ውድነት ለሚጠበሰው፣ ለተሰደደው ለተፈናቀለው ኢትዮጵያዊ እንድ አመት በሲኦል የቀናትና የወራት መቁጠሪያ እንደሚለካ ዘመን እጅግ የረዘመ የስቃይ ግዜ ነው።
የዋልድባ መነኩሳት ገዳማችን አትድፈሩ አታፍረሱ በማለታቸው እየተገረፉ ለዘመናት ፈጣሪያቸውን ከሚማጸኑበት ለሃገርና ለህዝብ ምልጃ ከቆሙበት ገዳም በዘር መመዘኛ እየተለዩ እንደቆ ሻሻ ተጠርገው የተባረሩበት ፣ እምነታችን አትንኩ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮችና መሪዎቻቸው በሃሰት ክስ ተመስርቶባቸው ወህኒ መውረዳቸው አንሶ ወንድሞቻችን ይፈቱ በማለት ሰላማዊ ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖቻቸን በወያኔ ነፍሰ- ገዳዮች በአረመኔያዊ ጭካኔ የተጨፈጨፉት በዚሁ አመት ነው። ወያኔ በህዝብ መሃከል በዘራው የዘር መርዝ የተነሳ በሽዎች የሚቆጠሩ አማሮች ከጉራ ፈርዳና ከቤንሻንጉል፣ ኦሮሞዎች ለዘመናት ከኖሩበት ምስራቅ ሃረርጌ አካባቢ እንዲፈናቀሉና በገዛ ሃገራቸው መድረሻ ቢሶች እንዲሆኑ የተደረገው በዚህ አንድ አመት ውስጥ ነው። ጋምቤላዎች ሙርሲዎች አፋሮችና ሌሎችም ብሄረሰቦችና ማህበረሰቦች የተጨፈጨፉበት፣በልማት ስም ለመጡ የውጭ ወራሪዎችና ወያኔ ለፈጠራቸው ቱጃሮች ቦታ እንዲለቁ ተደርጎ ቀደምቶቻቸው ለዘመናት ከኖሩባቸው ቀየዎች እንዲነቀሉ ተደርገው እንደ አልባሌ ነገር የትም እንዲበተኑ የማድረጉ ሂደት ከመቼውም በላይ ተጠናክሮ የቀጠለው በዚሁ አመት ነው። በዚሁ አንድ አመት በወያኔ የሃገሪቱ ገዥዎች በህዝብ ላይ የተፈጸመው ጭካኔና ወንጀል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ይህ ወያኔ ሰራሽ ሃገር በቀል የውርደትና የስቃይ ህይወት አልበቃ ብሎ ወያኔ ከሳውዲ የጨለማ ዘመን ገዥዎች ጋር በመተባበር ወንድሞቻችን በሳውዲ አውራ ጎዳናዎች ላይ እንዲታረዱ እህቶቻችን በቡድን በተደራጁ የሳውዲ ጎረምሳዎች እንዲደፈሩ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ለኢትዮጵያውያን ያለውን እጅግ የከረረ ጥላቻ በአደባባይ ያሳየበት አመት ነው። እንዲህ አይነቱ የጅምላ ግፍና ውርደት ከመከሰቱ በፊት ህዝባዊ ሃይሉ በአረብ ሃገር በባርነትና በስደት የሚገኙ እህትቶቻችንን ወንድሞችችን ስቃይ ስቃዩ አድርጎ በመውሰድ “ላንቺ ነው” በሚለው ድርጅታዊ መዝሙሩ “በባለጌ አረቦች መዳፍ ውድ ክብራቸው ለጎደፈው እህቶቻችን፣ በአረቦች የባርነት ቀንበር ጀርባቸው ለጎበጠው ወገኖቻችን እንደርስላችኋለን፣ የተሰባሰብነው ደማችን የሚፈሰው የመከራ ቀናችሁን ለማሳጠር ነው” የሚል ቃል ኪዳኑ ሰጥቶ ነበር። የድርጅታችንን ምስረታ አንደኛ አመት ስናከብር ልባችንን ደስታ ሳይሆን ሃዘን እንዲሞላ የሚያደርገው ይህ ቃል ኪዳናችን ለማክበር የጀመርነው ጉዞ ከድርጅት ምስረታና ከድርጅታዊ ዝግጅት አልፎ በኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻና ንቀት የተነፋውን የወያኔን እብሪት በማስተንፈስ የወሰዳቸው ተጨባጭ የአለኝታነት እርምጃዎች ባለመኖራቸው ነው።
ምንም እንኳን ግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል እራሱን እንደ ድርጅት አቁሞ ኢትዮጵያውያንን አሰባስቦ መራራው ትግል የሚጠይቀውን የፖለቲካ የወታደራዊ ስልጠናና ትጥቅ አስታጥቆ በወያኔ ላይ ለመዝመት የጀመረውን ጉዞ የሚያስቆመው ምድራዊ ሃይል እንደሌለ ብናውቅም የህዝብ ስቃይ ለግዜው መቀጠሉ የህባዊ ሃይሉን አባላት ማሰቃየቱ አልቀረም። በወያኔ ግፈኛ አገዛዝ የተንገፈገፈው ወገናችን ህዝባዊ ሃይሉ የወያኔን አገዛዝ እድሜ የሚያሳጥሩ ፈጣን እርምጃዎችን እንዲወስድ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ እንደሆነ እናውቃለን። ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች በተጠንቀቅ እንደቆሙ እናውቃለን። እነዚህ ዜጎች ከሁሉም የእምነት የቋንቋ የጾታ የእድሜ የኑሮና የማህበረሰብ ስብጥር የሚያካተቱ እንደሆኑ እናውቃለን። በሃገሪቱ ታሪክ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የወታደር ልብሱን እየጣፈ እንዲለብስ፣ የወታደር ጫማውን መቀየሪያ አጥቶ ሸበጥ እንዲያደርግ የተገደደውን፣ የወያኔ ጀነራሎች በስልጣንና በዘረፋ ሲያብጡ በድህነት እንዲሟሽሽ የተፈረደበት የሃገሪቱ ሰራዊት በዘር በእምነት ሳይለያይ ከህዝባዊ ሃይሉ ጎን ለመቆም አሰፍስፎ የቆመ እንደሆነ እናውቃለን። ይህ ሃገራዊ እውነታ ለህዝብ የገባነውን ቃልኪዳን የለምንም ጥርጣሬ ማስከበር እንደምንችል በሙሉ ድፍረት እንድናውጅ የሚያስችለን ሃቅ ነው።
የወያኔ ጀንበር እየጠለቀች የኢትዮጵያ ህዝብ ጀንበር እየፈካች የመሄዱ ጉዳይ እንደማይታጠፈው የመንጋትና የመምሸት የተፈጥሮ ህግ ነቅነቅ የማይል እንደሆነ ግንቦት7 ጠንቅቆ ያውቃል። እውቀታችን ልዩ ጥበብ የሚጠይቅ ኣይደለም። ግፍ ፍትህን አሸንፎ፣ እውነት በሃሰት ተደፍቃ፣ ጥላቻ ፍቅርን፣ አድሎ እኩልነትን፣ ሃገራዊ ክህደት ሃገር መውደድን፣ ባንዳነት አርበኛናትን ለዘላላሙ ቀብረው የሄዱበት የሃገራችንና የሰው ልጆች ታሪክ የለምና የወያኔን አይቀሬ ሞት ለመተንበይ ልዩ ጥበብ አያሻንም። ይህን እኛ ብቻ ሳንሆን በዘረፋና በጥላቻ የደነዘዘ ህሊና ያዳበሩት የወያኔ ባለስልጣናትም ያውቁታል። ያለእኔ ጀግና የለም፣ ያለእኔ አልሞ ተኳሽ የለም በሚል እብሪት በመጻደቅ የሚታወቁት ወያኔዎች በመቶ ሽዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች ተከበው፣ በታንክ በአይሮፕላን በሚሳይል ታጅበው ከሚኖሩበት ቤተመንግስትና ቪላዎች ውስጥ ብርክ እንዲይዛቸው ያደረገው ለመሆኑ፣ ሳር ቅጠሉ ግንቦት ሰባት እየመሰላቸው ሲበረግጉ እንደሚያመሹ፣ የግንቦት ሰባት አባላት እያሉ ከድርጅታችን ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች እያሰሩ ሲያሰቃዩ ፣ ከምላሳቸው ላይ ግንቦት 7 የሚል ስም ተፈናጦባቸው እንደሚውሉ በራሳቸው ሚድያ ወያኔዎች ራሳቸው እያሳዩን እያስደመጡን ነው። ከዚህም አልፎ በዚህ አንድ አመት ውስጥ የህዝባዊ ሃይሉን መሪዎች በመግደል ድርጅቱን ለማኮላሸት ይቻላል በሚል ወያኔ የላካቸው ነፍሰ ገዳዮችና ድርጅቱን ከውስጥ ለመቦርቦር ያሰማራቸው ሰርጎገቦች ተራ በተራ ተልእኳቸው እየከሸፈ በህዝባዊ ሃይሉ እጅ እየወደቁ ወይም ተልእኳቸው እንደማይሳካ ሲረዱ እየፈረጠጡ ወደ ወያኔ ሲመለሱ አይተናል።
No comments:
Post a Comment