Friday, December 6, 2013

በቦንጋ መምህራን አድማ ሊጠሩ ነው

esat

ህዳር (ሃያ ሰባ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በከፋ ዞን በቦንጋ ከተማ የሚገኙ መምህራን ፣ መንግስት ለአባይ ግድብ በማለት ያለፈቃዳቸው የቆረጠባቸውን ደሞዝ በአስቸኳይ ካልመለሰ ሰኞ የስራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
መምህራኑ ዛሬ ወርሀዊ ደሞዛቸውን ለመቀበል ወደ ባንክ ሲሄዱ ለአባይ ግድብ በሚል ደሞዛቸው ተቆርጦ ተሰጥቷቸዋል። በሁኔታው የተበሳጩት መምህራን ወደ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሲያመሩ መስተዳድሩ ያዘዘው በመሆኑ ምንም ማድረግ አንችልም የሚል መልስ ተሰጥቷቸዋል። መምህራኑም  አፋጣኝ መልስ የማይሰጠን ከሆነ፣ ከሰኞ ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ እናደርጋለን በማለት ለመስተዳድሩ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የመስተዳድሩ ባለስልጣናት በበኩላቸው፣ ውሳኔውን የሚቃወም መምህር ስራውን በራሱ ፈቃድ እንደለቀቀ ይቆጠራል በማለት የማስፈራሪያ ደብዳቤ ልከዋል።
ከዚህ ቀደም በጋሞጎፋ ዞን የሚገኙ መምህራን ተመሳሳይ ተቃውሞ በማሰማታቸው የተቆረጠባቸው ደሞዝ በፍጥነት እንዲመለስላቸው መደረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment