እንደሚታወቀው የኢህአዴግ አገዛዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጸረ ዲሞክራሲ አካሄዱ እየባሰበት የመጣና መሠረታዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ማፈኑን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ በቅርቡ በአንድነትና በመኢአድ ፓርቲ ላይ አገዛዙ በሚያዝዛቸው የተቋማት ኃላፊዎች ቀጭን ትዕዛዝ የፓርቲዎቹ ሕልውና ለጥቂት ግለሰቦች ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ይህ ዓይነቱ ህገ-ወጥ ድርጊት መቼዉም ቢሆን ተቀባይነት አይኖረውም! ለአገራችን የሠላማዊ የስልጣን ሽግግር ከባድ መሠናክል ሊሆን እንደሚችል ሁሉም ይገነዘባል ብለን እናምናለን፡፡ የኢህአዴግ የምርጫ ቦርድ እንዲህ ዓይነቱን ክፉ ስራ ሲወስን የአገራችንን የረጅም ሠላም አይተው ሣይሆን በአገዛዙ ቁንጮ ሰዎች በመታዘዝ በተቋም ስም የሚሠሩት የማደናገር የድንቁርና ተግባራቸዉ አንድ አካል ነው ብለን እናምናለን፡፡ ማህበራችን ይህን ድርጊት እጅጉን ያወግዛል። በመሆኑም ድርጊቱን በጋራ እንቃወማለን።
በምርጫ ቦርድ ስም የተወሰነው ህገ-ወጥ ውሣኔ ምክንያት መላ የአንድነትና የመኢአድ አባላት የፖለቲካ እንቅስቃሴአቸው ተገድቧል፡፡ ይሁን እንጂ ለአገራቸው ካላቸው ፅኑ ፍቅር አኳያ ትግሉን ለማስቀጠል ከሠማያዊ ፓርቲ ጋር አብሮ ለመሥራት የአባልነት ፎርም በመሙላት ትግሉን ቀጥለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ የአባላት ቆራጥ ውሣኔ ሊበረታታና ሞራል ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለን እናምናለን! እኛም በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የሁለቱ የድጋፍ ማህበራት ሙሉ በሙሉ ድጋፋችንን እንደምንሰጥ እናረጋግጣለን፡፡
ስለሆነም በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የአንድነትና የሠማያዊ የድጋፍ ማህበራት በጋራ በኮሜቴ ደረጃ ተዋቅረን በዋና ዋና ጉዳዬች ላይ ማለትም በፋይናንስ፤ በእስረኞች ጉዳይ እና በዲኘሎማሲው ዙሪያ ሙሉ በሙሉ በትብብር አብረን እየሠራን የሰማያዊ ፓርቲንና ሌሎች በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በጋራ ድጋፍ ለመስጠት ውሣኔ አሣልፈናል፡፡ በቀጣይም በጋራ የኮሚቴ ውይይቶችን እያደረግን ለሰማያዊ ፓርቲ የሚያስፈልጉ የሞራልና የማቴሪያል ርዳታ እንደምንሰጥ እናረጋግጣለን፡፡
የሰማያዊና የአንድነት ሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ማህበራት
የካቲት 19 2007 ዓ/ም
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39330#sthash.Jbph1yVo.dpuf
የሰማያዊና የአንድነት ሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ማህበራት
የካቲት 19 2007 ዓ/ም