Tuesday, June 30, 2015

ግብረሰዶም እና መፅሃፍ ቅዱስ (ከTeaching of EOTC የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ)

“ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ” ሮሜ. 1÷22
በዚህ ዘመን ግብረ ሰዶማዊነት እንደ ጥሩ ነገር እየታየ በመምጣቱ ጠዋትና ማታ በተለያዩ ማስ ሚዲያዎች፣ ድረ ገጾች፣ ፊልሞች፣ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ይቀነቀናል፤ ይሰበካልም፡፡ አንዳንዶችም ከሰው ልጅ ሥልጣኔ ጋር አብሮ የመጣ አድርገው ሲመለከቱት እና ሲያናፍሱት እናስተውላለን፡፡
በሰለጠነው ዓለም በወንድና በወንድ መካከል ያለው የግብረ ሰዶማዊ ግንኙነት (Gays) በሴትና በሴት መካከል ያለው የግብረ ሰዶማዊ ግንኙነት (Lesbians) እንደ ጥሩ ነገር እየታየ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊነት እያገኘ መጥቷል፡፡ በርካታ ሀገሮች የወንድ ለወንድ እና የሴት ለሴት ጋብቻን ከፈቀዱ ሰንብተዋል፤ በሒደት ላይ ያሉም ብዙ ናቸው፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ አንዳንድ የእምነት ተቋማትም/ፕሮቴስታንት እና ካቶሊክ ድርጅቶች/ ከመሪዎቻቸው ጀምሮ በዚህ ግብረ ሰዶማዊ ግብር ስለቆሸሹ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ግብረ ሰዶማዊነትን ደግፈው ሲሰብኲ እንዲሁም ወንድ ለወንድ ሲያጋቡ ታዝበናል፡፡ ይህ አስደንጋጭ እና አሳፋሪ ክስተት ብዙዎቻችንን ሊያስደነግጠን ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማዊነት ዛሬ የተጀመረ ክፉ ግብር ሳይሆን ጥንትም የነበረ ብዙዎችን ያረከሰ ነውር እና አስጸያፊ ተግባር መሆኑን ይመሰክራል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ በሆነው በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ይናገራል፡፡ የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ግብረ ሰዶማውያን ነበሩ፡፡ ሰዶምና ገሞራ በዮርዳኖስ ሸለቆ የተቆረቆሩ ከተሞች ነበሩ፡፡ በእነዚህ ሁለት ከተሞች ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ግብረ ሰዶማውያን ማለትም ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር ዝሙት የሚያደርጒ ይህ ኃጢአትም በእነርሱ ይበዛ ስለነበር ስያሜው የቦታውን ስም በመያዝ ግብረ ሰዶም ተባለ፡፡ በዘመናት ሁሉ ይህን ኃጢአት የሚሠሩ መጠሪያ ሆኖ አገለገለ፡፡ ዛሬም በግብር የሚመስሉአቸው ሰዎች ግብረ ሰዶማዊ ወይም ሰዶማውያን እየተባሉ ይጠሩበታል፡፡ የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር የሚፈጽሙት ዝሙት አጸያፊ ስለነበር እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ወሰነ፡፡ (ዘፍ. 18÷20፣ ዘፍ.19÷5-9)፡፡ ሁለት መላእክትን ወደ ሰዶም ላከ፡፡ ሁለቱ መላእ ክት የእግዚአብሔር ሰው እና ከሰዶማዊነት ግብር ንጹሕ የነበረውን ሎጥን ከከተማው እንዲወጡ ካደረጉ በኋላ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን በእሳትና በዲን አጠፋ፡፡ (ዘፍ.19÷10-26) ሰዶምና ገሞራ አሁን በጨው ባሕር እንደተሸፈኑ የሥነ ምድር ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ሰዶምና ገሞራ የክፋት ሁሉ የፍርድም ምሳሌ በመሆን ተጠቅሰዋል፡፡ (ኢሳ. 1÷9-10፣ ኢሳ. 3÷9፣ ኤር. 23÷14፣ ሰ.ኤ.4÷6፡፣ ሕዝ. 16፡46፣ ማቴ.10÷15፣ ራእ. 11÷8)
ሰዶማዊነት ነውር ነው፡-
መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማዊነት ነውር እና አጸያፊ እንደሆነ ይመሰክራል፡፡ ነውር የሆነበትም ምክንያት ይህ ነው፡፡
ሀ. እግዚአብሔር የመሠረተውን የጋብቻ ሥርዓት ማለትም አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት የሚለውን ሕግ የሚያፈርስ በመሆኑ፤
ለ. በሁለት ተቃራኒ ጾታ ማለትም በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረገውን ተፈጥሮአዊ የግብረ ሥጋ ግንኙነት/መሳሳብ/ የሚያቆሽሽ አዲስ ልምድ ስለሆነ፤
ሐ. የሰው ልጅ ዘሩን የመተካት ከፊጣሪ የተሰጠውን መብቱን የሚገፋ (የሚያሳጣ) ተግባር በመሆኑ፤
መ. ሰዶማዊነት በአንድ ወንድ ወይም በአንዲት ሴት ብቻ የሚቆም ግብር ስላልሆነ፤ ወንዱ ብዙ ወንዶችን ሴቷ ብዙ ሴቶችን ሲለምዱ ለተለያዩ በሸታዎች ስለሚያጋልጥ፤
ሠ. ሰዎች ስለ ፍቅር ትክክለኛ ሥእል እንዳይኖራቸው እና በስሜት የሚነዱ ራስ ወዳዶች እና ሓላፊነት የማይሰማቸው ዜጎችን ስለሚፈጥር፤
ረ. የተለያዩ አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊ እና መንፈሳዊ ክስተቶችን ስለሚያስከትል በእግዚአብሔር የተናቀ እንዲሁም የተጠላ ግብር ነው፡፡ከተፈጥሮ ሥርዓትና ሕግ ውጪ በመሆኑ በኅብረተሰቡም ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ማኅበራዊ መገለልን የሚያስከትል ክፉ ተግባር ነው፡፡ይህ ክፉ ግብር ወንድ ከወንድ ሴት ከሴት ጋር ብቻ ሳይሆን ከእንስሳትም ጋር ግንኙነትእንዲፈጽሙ በር የሚከፍት ነውረኛ ሕይወት ነው፡፡
“ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው፡፡” (ዘሌ. 30÷13)
“የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ፡፡” (ዘፍ. 13÷13)
“እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጒና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸው የነበሩ ከተማዎችም በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል፡፡” (ይሁዳ. ቁ. 7)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜና በቆሮንቶስ መልእክቱ ግብረ ሰዶማዊነትን “እስነዋሪ”፣ “ለባሕርይ የማይገባ”፣ እንዲሁም “ከተፈጥሮ ሕግና ሥርዓት ውጪ” እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቶ ያስተምራል፡፡ በዚህ ሰዶማዊ ግብር ኃጢአት የሠሩት ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም እንደሆኑ ይናገራል፡፡
“ . . . ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርድ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኲስነት አሳልፎ ሰጣቸው . . ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶች መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ፡፡” (ሮሜ. 1÷24-27)
“. . . ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን አትሳቱ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣኦትን የሚያመልኲ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚያደርጒ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፡፡” (ቆሮ. 6÷9-10)
ወጣቶች “ቀላጭ” ማለት ወንዳገረድ ለጾታው የማይገባ ዝሙትን ለመፈጸም እንደ ሴት ሆኖና ከወንድ ዘርን የሚቀበል ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም ሴት ከወንዳ ወንድ ሴት ጋር ዝሙት ስትፈጽም ‹‹ቀላጭ›› ትባላለች፡፡
ማጠቃለያ፡-
ወንድሞችና እህቶች ግብረ ሰዶማዊነት በእግዚአብሔር የተጠላ ክፉ ግብር መሆኑን ተገንዝባችሁ ራሳችሁን ከዚህ ክፉ ተግባር ጠብቁ፡፡ ብዙ ንጹሐን ሰዎች በእነዚህ ክፉ ሰዎች እንዳይበላሹና ሰዶማውያን እንዳይሆኑ እውነታውን ማስተማር ግንዛቤ መፍጠር የሁላችሁም ሓላፊነት መሆኑን አንዘንጋ፡፡እንዲሁም በዚህ ህይወት ያሉትን ሰዎች በተቻለን መጠን መክረን ከዚህ ህይወት እንዲወጡ መፀለይ ያስፈልገናል እንዲሁም እዚህ ህይወት ውስጥ ያሉትን ሰዎች እግዚአብሔር መሀሪ እና ይቅር ባይ ፍቅር መሆኑን አምነው በንስሀ እንዲመለሱ ጥረት እናድርግ ፡፡እግዚአብሔር አምላካችን አገራችንን ቤተክርስቲያናችንን አለማችንን ከዚህ ክፉ መንፈስ ይጠብቅልን ከአለማችን ይህንን ክፉ መንፈስ ያጥፋልን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡-
1.ግብረ ሰዶማዊነት እና የሴቶች ክህነት/ብፁ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የቀድሞ ፓትርያሪክ እንደፃፉት ትርጉም ታደለ ፋንታ/ዲ/ን/
2. አባ ሳሙኤል ሰዶማውያንና የኃጢአት ደሞዝ (1998) ዓ.ም አዲስ አበባ፡፡እና ሁለተኛ እትም
3.የተለያዩ ድህረ ገፆች

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!