Saturday, April 26, 2014

ዝምታችን ይበቃል......!!!!


<< ቀለል ብሎ ከበድ ያለ ጥያቄ፡- ከእኔ ምን ይጠበቃል!? >>
በሀገራችን ኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ በኃይል የተጫነው እራሱን "መንግሥት" ብሎ የሚጠራው ሕወሓት/ኢህአዴግ፤ ለ"ሀገር"/ድርጅት ደህንነት፣ መከላከያ እንዲሁም ፖሊስ በሚሰጠው የቀጥታ ትዕዛዝ እነሆ አማራጭ መንገድ አለን የሚሉ የፖለቲካ አመራርና አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም ንፁሐን ዜጎችን አስከፊውን የቀይ ሽብር እንዲሁም በጀርመን የናዚን ዘመን በሚያስታውስ ሁኔታ ከየመንገዱ እና ከየቤታቸው ከሕግ በላይ ሆኖ በማፈስ ወደ ከርቸሌ እንዲሁም ወዳልታወቀ ቦታ እየወሰዱ ድብደባ፣ ወሲባዊ ትንኮሳ እና አካላዊ ሥቃይ በማድረስ ላይ መሆናቸው ያደባባይ ምሥጢር ነው።
አንድ የውጭ ወራሪ ኃይል እንኳን በወረረው ዜጋ ላይ ሊያደርሰው የማይችለውን ዓይነት ውርደት እና ሥቃይ በሙስናና በሞራል ዝቅጠት የላሸቀው የሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በገዛ ዜጎቹ ላይ (የከፍተኛ አመራሮች ዜግነት ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ሆኖ) እያደረሰ መገኘቱን ይህ ትውልድ እንዴት እንቀበለዋለን? ምንስ እናደርጋለን?
እነሆ እስከዛሬ ድረስ ሕወሓት ሕግ አውጪ፣ ዳኛ፣ እንዲሁም ፖሊስ በሆነባቸው ተቋማት አማካኝነት አሸባሪ ተብለው እስር ቤት የሚማቅቁ ዓለም እልል ብሎ የሸለማቸው ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ የፖለቲካ አመራሮችና አባላትን ጨምሮ ሰሞኑን በገፍ እየተጋዙ ያሉትን ቆራጥ፣ ወጣት-የነብር-ጣት ወንድሞች እና እህቶች ሕወሓት 23 ዓመት ሙሉ ለመሸርሸር ወጥሮ የደከመበትንና የኢትዮጵያችንን እንዲሁም የዜጎችን መብት፣ አንድነት እና ክብር ለማስመለስ መሥዋዕትነት እና ዋጋ እየከፈሉ ነው።
አሁንም ጊዜው በጣም አልረፈደም፣ ዝምታችን ይበቃል። ጎጂ ባህል የሆነውን ወደሌሎች ጣታችንን መቀሰር፣ እንዲሁም ስህተት ቢሰሩም እንኳን ከዚህ ቀደም ሠርተው የወደቁትን (ያልተሳካላቸውን) እንዲሁም እየሠሩ ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች፣ ግለሰቦች በተደጋጋሚ መተቸት የሰነፍ ቀዳሚ መለያና አጉል ምክንያት መሆኑን ተገንዝበን፤ "ከእኔ ምን ይጠበቃል?" ብለን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የምንችለውን ጠጠር ለመወርወር ቆርጠን መነሳት ያለብን ትላንት ቢሆንም ቅሉ፤ አሁንም ግን ዕድሉ አለና ይበቃል እንበል። ዛሬ ግን የመጨረሻው ይመስላል።
የምንችለውን ሁሉ በማድረግ፡-
>> ይህን አስከፊ የሕወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት ከኢትዮጵያችን ጫንቃ እናላቅቅ፣
>> ግፈኞቹን በሕግ ፊት እናቅርብ፣
>> ከሁሉ ጠቃሚ የሆነውን በሀገራችን ብሔራዊ ዕርቅ እንዲካሄድ እንስራ፣
>> ይዘታቸው ወደ ሕወሓት የግል ንብረትነት የተቀየረውን የመንግሥት (የሕዝብ) ተቋማት እንደኛ ለመመሥረት አስተዋፅዖ እናበርክት ወዘተርፈ...
ጎበዝ፤ ይህን ሁሉ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በተደራጀ መልኩ ብቻ በመሆኑ፤ ለውጥ አመጣለሁ ብለን በምናምንበት ማንኛውም አማራጭ የፖለቲካ ኃይል፣ የዴሞክራሲ ግንባታ ተቋም፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅት፣ የማኅበረሰባዊ ድርጅት ውስጥ ወዘተርፈ . . . በመሳተፍ ጠብ የሚል ነገር እናምጣ።
ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች፣ ወደልጆችዋም ጭምር!
ከክብሩ ደመቀ

Wednesday, April 23, 2014

የኤርትራ፣ የሱዳን፣ የሶማሊያ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው ሲገቡ የሚገባቸው ነገሮች ይሰጣቸዋል፡፡


በጎንደር 30 ሺህ ቤቶች እንደሚፈርሱ ታወቀ – ‹‹በከተማዋ ውጥረት ነግሷል››

ጎንደር፡- በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ከ30 ሺህ በላይ ቤቶች የተገነቡባቸው ሶስት ሰፈሮች ሊፈርሱ መሆኑን በስፍራው የሚገኙ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች አስታወቁ፡፡ በከተማዋ ቀበሌ 18 ከተመሰረቱ ከ7 አመት በላይ የሆናቸው አርማጭሆ፣ ገንፎ ቁጭና ህዳሴ የተባሉ ሰፈሮች ውስጥ የተገነቡ ከ30 ሺህ የሚልቁ ቤቶችን እንዲያፈርሱ ለነዋሪዎች ትዕዛዝ በተሰጠበት ስብሰባ የተካፈሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡በስብሰባው ላይ ነዋሪዎቹ፣ ‹‹ህገ ወጥ ከሆነ ያኔ ሕገ ወጥ ነው ልትሉን ይገባ ነበር፡፡ ህገ ወጥ ነው ከተባለስ ይህ ሁሉ ዜጋ በርካታ ገንዘብ አፍስሶ ቤት ከሰራና ለ7 አመት ከኖረ በኋላ ህጋዊ ማድረግ አይቻልም ነበር? ይህም ካልሆነ ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቶንና ሰፊ ጊዜና ተለዋጭ ጊዜ ተሰጥቶን

እንጂ በድንገት ተነሱ ልትሉን አይገባም›› የሚል መከራከሪያ ማንሳታቸው ታውቋል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹እኛ የራሳችን አገርና ቦታ ላይ የምንገኝ ዜጎች ነን፡፡ ቤታችንን የሰራነው ማንም ሳያግዘን በራሳችን ጥረት ነው፡፡ የኤርትራ፣ የሱዳን፣ የሶማሊያ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው ሲገቡ የሚገባቸው ነገሮች ይሰጣቸዋል፡፡ እኛ ግን ያለምንም ቅድመ ዝግጅት፣ ካሳና ተለዋጭ ታ ሳይሰጠን ቤታችሁን አፍርሱ መባላችን ዜግነታችንም ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው›› ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡
የከተማዋ ባለስልጣናት በበኩላቸው፣ ‹‹መንግስት ህገ ወጥ ነው ብሎ የሚያምነውን ሁሉ ማፍረስ መብቱ ው፡፡ አይደለም ጎንደር አዲስ አበባ ውስጥም ቤት ይፈርስባቸዋል፡፡›› በሚል ለማሳመን ሞክረዋል፡፡ ‹‹በዚህ ጊዜ ውስጥ ልጆቻችን ይዘን የት ልንሄድ ነው… ሽማግሌዎችስ የት ይደርሳሉ?›› የሚሉ ሌሎች አንገብጋቢ ጥያቄዎችን አንስተው አጥጋቢ ልስ ያላገኙት ነዋሪዎቹ ከባለስልጣናቱ ጋር ባለመስማማታቸው አብዛኛዎቹ ‹‹ማፍረስ ከተፈለገ እናንተው አፍርሱት እንጂ እኛ አናፈርስም፡፡›› በሚል ስብሰባውን አቋርጠው መውጣታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ነዋሪዎቹ እስከ ሚያዚያ 7 አፍርሱ፣ ካለፈረሳችሁ እኛው ስለምናፈርሰው እቃችሁን አውጡ ቢባሉም አሁንም ድረስ በአቋማቸው ጸንተው የሚመጣውን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ምንጮቻችን ጨምረው ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ህዝቡ በክረምት ተፈናቅሎ የት ይደርሳል በሚልና እንዲፈርስ በሚፈልጉት
የከተማው ባለስልጣናት መካከል ውጥረት መንገሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ህዝብን አሳምጻችኋል የተባሉ 12 ሰዎች መታሰራቸውና ከጎንደር በተጨማሪ ቆላ ድባና ሌሎች ከተሞችም ቤቶች እንዲፈርሱ ትዕዛዝ መሰጠቱን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ ከሰሞኑ በባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎችን ከማፈናቀል ሂደት ጋር በተገናኘ ህዝብና ፖሊስ በመጋጨታቸው የሰው ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
Ze-Habesha 

Monday, April 14, 2014

በኖርዌ ያሉ ኢትዮዽያውያን የወያኔን የስለላ መረብ በመቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

በ11-4-2014 በኖርዌ ያሉ ኢትዮዽያውያን የወያኔን የስለላ መረብና ኖርዌ በስደተኛው ላይ ያላትን ፖሊሲ በመቃወም    የተቃውሞ ሰልፍ አረጉ።  23 ዓመት እራሱ መራጭ እራሱ ተመራጭ ሆኖ በጠመንጃ አፈሙዝ ህዝቡን እያንቀጠቀጠ የኖረው ወያኔ

አንድ ቀን ሕዝብ በቃኝ ብሎ አንቅሮ እንደሚተፋውና ንብ ሆኖ ለነፃነቱ እንደሚነሳ ማወቅ ነበረበት።
ግን አልሆነም ዜጎች እንደዜጋ በሐገራቸው መኖር ቀርቶ በስደትም ሰላማቸውን ማግኘት አልቻሉም።
እስርና እንግልት፣ረሐብና ሰቆቃ፣ስደት የእያንዳንዱ እጣ ፋንታ ሆነ፤በወያኔ ዘመን ሰው ብቻ አይደለም መሬትም መሰደድ ጀምሮ የግል ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል የኢትዮዽያን ለም መሬት ለሱዳን በመሸጥ ላይ ይገኛል
ኢትዮዽያንና ኢትዽያዊነትን ያሉ ሁሉ አሸባሪ እየተባሉ በየእስርቤቱ ታጉረው እጣ ፈንታቸው እስርና እንግልት ሆነ
ሐገራቸውን ጥለው በባሕርና በየብስ አቆራርጠው የሞተው ሞቶ የተረፈው በአለም ዙሪያ ተበትኖ ጥገኝነት  በመጠየቅ ይኖራል.
በዚሕም የተሳካላቸው ጥቂቶች ሲሆኑ ባብዛኛው ወያኔ ለውጩ አለማት በሚያሳየው ሁለተኛው ፊቱ ምክንያትና ምእራባውያን ከሐገሪቱ ከሚያገኙት ጥቅም የተነሳ ሐገርህ ዲምክራሲ ነው እየተባለ ፍትሀዊ ያልሆነ መልስ እየተሰጠው በመጉላላት ላይ ይገኛል።
ያም ሆኖ የሐገሩ ጉዳይ በደም ስሩ ሰርጎ የገባው ኢትዮዽያዊ ሁሉ ጠዋት ማታ ኢትዮዽያዬ እያለ ይጮሀል። ይህ የህዝብ ቁጣ ያስፈራው ወያኔ ያለ የሌለ የሐገሪቱን ኢኮኖሚ እየመዘበረ ዜጎችን ይሰልላል ያሰልላል፣አልፎ ተርፎም ዜጎችን ከመሰሎቹ ጎረቤት ሐገሮች ድረስ በመሄድ ጎትተው እስርቤት ያስገባሉ።
ይህንን ለመቃወምና ለማውገዝ ነበር የኢትዮዽያ ስደትኞች ማህበር በኖርዌ ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅቶ ኢትዮዽያውይኑ ዛሬም ስለ ሐገራቸው ሊጮሁ የወጡት፤ ሰልፈኞቹ ድምፃቸውን እንዲህ በማለት ነበር ድምፃቸውን ያሰሙት እኛ ስደተኞች እንጅ ወንጀለኛ አይደለንም፣ኖርዌ ለማፊያው ወያኔ የምታደርጊውን እርዳታ አቁመሽ ከኢትዮዽያ ሕዝብ ጋር ቁሚ፣ወያኔ የሚያደርገውን ተግባር እናወግዛለን፣ሼም ኦን ዩ ሳውዝ ሱዳን ኦኬሎን አሳልፈሽ የሰጠሽ፣ወያኔ አሸባሪ ነው፣ለውጥ እንፈልጋለን፣ኖርዌ የዩኤንን ህግ ታክብር የሚሉትን የመሳሰሉ ሲሆን
በሰልፉ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የኢትዮዽያ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ተወካይ አቶ ዳንኤል የወያኔን ጀሌዎች የማጋለጡ ስራ በሚገባ እየተሰራበት መሆኑን ሲገልጡ ሰልፈኛው በጭብጨባ የተቀበላቸው ሲሆን የስደተኛ ማህበሩም ተወካይ ኖርዌ ነፃ እንድታወጣን ሳይሆን ለወያኔ የምትሰጠውን እርዳታ አቁማ ድጋፍ እንድትሰጠን ነው፤ በተጨማሪም ኖርዌ አቶ ኦኬሎን ታስለቅቅ በማለት  ተጠይቃለች። በሰልፉ ላይ የኖርዌ ሊብራል ፓርቲ ተወካይ ከሰልፈኛው ደብዳቤ ተቀብለው መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን
የኖዋስ ፣አንቲረሲስት ተወካዮችም እንዲሁ ይዘውት የመጡትን መልክት ለሰልፈኛው አስተላልፈዋል።
ከዚያ በቀጥታ ወደሶፊን በርግ ሎካል አዳራሽ ሰልፈኛው አምርቶ ምሳ  ከተበላ በሁዋላ ኮሚቴው ካባላቱ ጋር ሰፊ ዉይይት ያደረገ ሲሆን የ፫ወር የስራ ሪፖርትም አቅርቦአል።
የኢትዮዽያ ስደትኞች ማህበር በኖርዌ

የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የዲያስፖራውን ሚና በተመለከተ በኖርዌይ ኦስሎ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ


በዲምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ  የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አዘጋጅነት አፕሪል ቅዳሜ 12/2014  በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ  የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የዲያስፖራውን ተሳትፎ በተመለከተ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ተካሄደ:: በሕዝባዊ ስብሰባው ላይ ቁጥራቸው ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች ከኦስሎ እና ከተለያየ ከተማ  በመምጣት በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን  የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ቡዙነህ ፅጌ የስብሰባው ተጋባዥ እንግዳ በመሆን ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል::
ሕዝባዊ ስብሠባው በኖሬጅያውያን የሰአተ አቆጣጠር ከቀኑ 15:00 እስከ ምሽቱ 21:00 ሰዓት የተካሄደ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ  አቶ አቢ አማረ በኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ አረመናዊ ስርአት በጭካኔ በግፍ ለተገደሉ እና በተለያዩ አስር ቤቶች በፖለቲካ ኣስተሳስባችው ምክንያት ያለወንጀላች የሚስቃዩ ውድ ኢትዮጵያዊን ወገኖቻችን በማስብ  በዚሁ ዘረኛ ቡድን አስቃቂ የኣካል ጉዳት ለተፈጸባቸው ኢትዮጵያዊን  የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማስደረግ ስብሰባውን አስጀምረውታል::

በመቀጠለም አቶ ዮሀንስ አለሙ የዴምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሊቀመንበር የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸው ስለ ዲምክራሲያዌ ለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አመሰራረት እና ስለ ድጋፍ ድርጅቱ አላማ በማብራራት የድጋፍ ድርጅቱ በአሁኑ ሰአት በሀገር ቤት በሰላማዊ ትግል የወያኔን መንግስት ለመጣል እየታገሉ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶችን እየረዳ እንደሚገኝ እና ከሀገር ውጭ ደግሞ የወያኔን መንግስት  በሁለገብ ትግል  ለማስወገድ እየሰራ ያለውን የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሴ ንቅናቄ የፖለቲካ ድርጅትን በግንባር ቀደምነት እየረዳ እንዳለ በመግለጽ  የወያኔን ዘረኛ ስርአት ለመጣል ሁሉም ሰው አስተዋጿ ማድረግ እንደሚጠበቅበት እና ማንኛውም  ኢትዮጵያዌ ዜጋ በሀገራችን የጋራ ጉዳይ ስለሆነው  የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ሀሳብ በመለዋወጥ ፣በመካከላችን ያሉትን ማንኛውንም የሃሳብ ልዩነቶች ወደ ኋላ በመጣል ፣ በመቻቻል፣ ሀገር እያፈረሰ እና ሕዝብ እያዋረደ ያለውን የዘረኛውን የወያኔን መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሁለገብ ትግል ለማስወገድ መረባረብ እንዳለበት አጽኖት ሰተው ንግግር አድርገዋል::
በመቀጠለም ዲምክራሲያዊ ለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ድርጅቶች መካከል አንዱ የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል የሆኑት አቶ ቡዙነህ ፅጌ የስብሰባው ተጋባዥ እንግዳ ሰፊውን ጊዜ በመውሰድ ከንጉሱ ስርአት ጀምሮ በደርግ መንግስት ዘመንም በሀገራችን የተደረጉ የፖለቲካ ንቅናቄዎችንና ለውጦችን አንድ በአንድ በመዘርዘር አሁን ካለው የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ጋር በማነጻጸር ሰፋ ያለ ትንታኔ ያቀረቡ ሲሆን አሁን ላይ ሀገሪቱን እየመራው ነው የሚለው የወያኔ መንግስት ከዚህ ቀድሞ ኢትዮጵያን ከመሩት ከሁለቱ መንግስታቶች ማለትም ከንጉሱም ከደርግም መንግስት ጋር ሲነጻጸር ፈጽሞ እንደማይገናኝ የወያኔ መንግስት ዘረኛና የዘረኝነት ፖለቲካ እያራመደ ያለ አረመናዊ መንግስት እንደሆነ አብራርተዋል::
የግንቦት 7  የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ቡዙነህ ፅጌ አክለውም ከወያኔ በፊት የነበሩ ሁለቱ መንግስታቶች ለውድቀት የዳረጓቸውን ምክንያቶች በመጥቀስ የወያኔን አንባ ገነናዊ መንግስት ለአፋጣኝ ውድቀት ሊዳርጉት ይችላሉ የሚሉትን ግልጽ ምክንያቶች በመዘርዘር አስቀምጠዋል:: አቶ ቡዙነህ በሁለት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማንሳት እና በማብራራ ከሕዝብ ውይይት እንዲያደርጉበት ለመወያያ ያቀረቡ ሲሆን እነዚህም
1, በሙስሊሙ ማህበረሰብ እና በወያኔ መካከል ያለው ግጭት
2, የህዳሴ ግድብን  በማስመልከት ያለው ተቃውሞ
ስለሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቃውሞ ሲናገሩ የሙስሊሙ ትግል በሁለት አመታት ውስጥ የተደረገው ሰላማዊ ትግል በጣም የተሳካና ወያኔ በቀላሉ ሊያዳፍነው ያልቻለው ሰላማዊ መብትን የመጠየቅ ትግል እንደሚያደንቁ በመናገር ነገር ይህ በሙስሊም ማህበረሰብ በኩል እየተደረገ ያለው ትግል እስከ አሁን ድረስ ከመንግስት በኩል ምንም አይነት መልስ ሊያገኝ እንዳልቻለ እና ወደፊትም ከወያኔ መንግስት በኩል ምንም አይነት መልስ ያገኛል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል:: ለዚህም ማስረጃው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከጠየቋቸው አራት የመብት ጥያቄዎች አንዱም ካለመመለሱ በተጨማሪ እስካሁን መሪዎቻቸውም በሃሰት ውንጀላ በእስር እየማቀቁ ያለፍርድ እየተንገላቱ መሆናቸው ነው፥፥
ነገር ገን አሁን እየሆነው ባለው ሁኔታ በእንደዚህ አይነት መንገድ እስከመቼ ድረስ የሙስሌሙ ትግል ይቀጥላል በማለት የተናገሩ ሲሆን አሁን እየሄደ ባለው አካሄድ የሙስሊሙ ተቃውሞ የትግል አቅጣጫውን እስካልቀየረ ድረስ ረጅም ርቀትን ትግሉ ሊቀጥል ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸው እና ነግር ግን የሙስሊሙ ጥያቄ ከእምነት መብት ጥያቄ ባሻገር ወደ የዜግነትን መብት ወደ ማስከበር መለወጥና መሸጋገር  እናደለበት በመናገር የሙስሊሙ ማእበረሰብ ጥያቄ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው  ትግሉ በዚህ መልኩ ሲቀጥል እንደሆነ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰተዋል:

በሁለተኛም የህዳሴ ግድብ በሚመለከት  ያቀረቡት ሀሳብ ወያኔ የራሱን የፖለቲካ ኪሳራና በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉን ግፍ በዕድገት ስም ለመሸፈን ያመጣዉ እንጂ ታቅዶበትና ለህዝቡ በማሰብ እንዳልሆነ በኢትዮጵያና በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉ ግፍ እንደ ማስረጃነት በማቅረብ ያብራሩ ሲሆን እንደ ምሳሌም ወያኔ ሃገራዊ የሆነ አላማ ይዞ ካለመነሳቱ አንፃር የሃገርን ድንበር አሳልፎ እስከመስጠት እየሄደ ያለበትን ሁኔታ ጠቅሰው ይህ አሰራር ደግሞ የዲክታተሮች ባህሪ እንደሆነ አብራርተዋል፥፥

የወያኔ መንግስት በህዳሴ ግድብ ሰበብ ምክንያት በማድረግ በመላው አለም ኢትዮጵያኖች በሚኖሩበት ሀገሮች በመዞር የዲያስፖራውን ቀልብ ለመውሰድ የሚያደርገው የአባይ ቦንድ ሽያጭ ሩጫ በዲያስፖራ ተቃዋሚዎች አማካኝነት በፍጹም እንዳልተሳካለት ይህንንም የወያኔ በአባይ ቦንድ ሽያጭ ስም ገንዘብ ዘረፋ በመቃወም ወያኔን አሳፍረው ከመለሱት መካከል በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች እንደሆኑ በማስታወስ  የዚህ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሰበብ የወያኔን መንግስት ወደ መጥፎ ውድቀት ላይ ሊጥለው እንደሚችል በማመን የወያኔ መንግስት በአሁን ሰአት ከግብጽ መንግስት ጋር እየገባ ያለው ሰጣ ገባ ለኢትዮጵያ መጥፎ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ንግግራቸውን አጠቃለዋል፥፥

በመቀጠልም አቶ ብዙነህ ባነሷቸው ነጥቦችና እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከስብሰባው ተሳታፊዎች ለቀረበላቸው በርካታ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሰፋ ያለ ውይይትም ተደርጓል፥፥ ከውይይቱም በማስቀጠል የዲምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዳንሄል አበበ የዲምክራሲያዌ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የአቋም መግለጫ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ድርጅታቸው ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል ፈጽመው እንደሚያወግዙ እና ዴምክራሲያዌ ለለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሁል ጊዜ ከግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሴ ንቅናቄ ጎን እንደሚቆም ቃል በመግባት የአቶ ቡዙነህ ፅጌን በኖርዌይ በመገኛት ለህዝቡ ለሰጡት ገለጻ አመስግነዋል፥፥
በዝግጅቱ መጀመሪያና ማጠቃለያ ላይ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል መዝሙር በመዘምራን የተዘመረ ሲሆን በየጣልቃው የተለያዩ የባህል ዘፈኖች በተወዛዋዦች ታጅቦ የቀረበ ሲሆን ጣእም ያለው ባህላዊ ምግብም በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የሴቶች ክፍል ተስተናግዷል፥፥ ስብሰባውን ተጀምሮ እስኪያልቅ አቶ ፍቅሬ አሰፋ መርተውታል::

በመጨረሻም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ለዝግጅቱ መሳካት የበኩላችሁን ላበረከታችሁና ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች ረዥም ርቀት በመጓዝ የዝግጅቱ ታዳሚ ለነበራችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን እና እንዲሁም የድርጅቱ አባላቶች ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን፥፥


ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

Sunday, April 13, 2014

ኢህአዴግ እንደ ናቡከደነፆር

በአንድ ወቅት የዓለም ገናና ንጉስ የነበረው የባቢሎን ንጉስ ናቡከደነፆር ለ43 ዓመታት ባቢሎንን ገዝቷል፤ በስተሰሜን ሶሪያ በምዕራብ በፍልስጤም እስከ ግብፅ ግዛቱን አስፋፍቷል፡፡ ይህ ንጉስ ህጎችን ከመቀፅበት ይደነግጋል፣ ይለውጣል፡፡ ለእሱ ስርዓት ተገዥ ያልሆኑትን ያስራል፣ ይገርፋል፡፡ ንጉስ ናቡከድነፆር በጣም የሚፈራ እና ኃይለኛ ንጉስ ቢሆንም ከመውደቅ ግን አልዳነም፡፡ ለማንኛውም የዚህ ንጉስ ታሪክና የሀገራችን መንግስት ስርዓት ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገሮች ስላሉ እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡
ንጉስ ናቡከድነፆር በዘመኑ በጣም የሚፈራ እና የማይደፈር እንደመሆኑ መጠን የፈለገውን የማድረግ መብት ነበረው፡፡ በዚህም መሰረት ነው የሌለባቸውንና መልክ መልከኞችን ጥበብና ዕውቀት የሞላባቸውን በብልሀት ዳኞችንና አስተዋዮች የሆኑትን በንጉሱም ቤት መቆም የሚችሉ ብላቴናዎችን በእስራኤል ልጆች ከነገስታቱ እና ከመሳፍንቱ ዘር ይመጣ ዘንድ ለጃንደራቦቹ አለቃ ለአስፋኔዝ ነገድ ዳንኤል 1,3,4፤ የተመረጡትም ወጣቶች ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ፡፡ በእርግጥም እነዚህ ወጣቶች ጤናማ አዕምሮና አካል እንዲሁም ጥልቅ ማስተዋል ጥበብና ዕውቀት ነበራቸው::
ንጉስ ናቡከደነፆር እነዚህን ወጣቶች ከባቢሎናውያን ስርዓት ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ ንጉስ የከላዳውያንንም ትምህርት ቋንቋ ያስተምራቸው ዘንድ ጃንደረቦቹን አዘዘ፡ ፡ ንጉሱም በእርሱ ዘንድ እንዲቆሙ ስለሚፈልግ ከንጉስ መጠጥና መብል በየዕለቱ እንዲወስድላቸው አዘዘ፡፡ ስማቸውንም ቀየረ፡፡ ንጉስ የእነዚህን ወጣቶች ስም የቀየረው በራሱ መስመር ለሱ እንዲስማማው እና የእሱ ተገዥ እንዲሆኑ ለማሳወቅ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ስማቸውንም ቢቀይረው የዓላማ ፅናታቸውን ግን መቀየር አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ናቡከደነፆር የግዛቱን አንድነት ለማጠናከር በማሰብ በዱር ሜዳ አንድ የወርቅ ምስል አቆመ፡፡ የምስሉ ርዝመት 60 ክንድ (27 ሜትር) ወርዱ 6 ክንድ (2.7 ሜትር) ነበር፡፡ ንጉስ በዚሁ ምስል የምረቃ ሰነ ስርዓት አዘጋጅቶ መሳፍንቱንና ሽማምንቶቹን፣ አገር ገዥዎቹን፣ አማካሪዎቹን፣ የህግ አዋቂዎችን ሰብስቦ ላሰራው የወርቅ ምስል የእምቢልታና የዘፈን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ተደፍተው እንዲሰግዱ፣ ካልሰገዱ ደግሞ በሚነደው የእቶን እሳት ውስጥ እንደሚጣሉ ተነገራቸው፡ ፡ ሙዚቃው መሰማት ሲጀምር ያ ሁሉ ባለስልጣን ተደፍቶ ሲሰግድ እነዚያ አስተዋይና ጥበበኞች ወጣቶች ግን ቀጥ ብለው ቆሙ፤ የወጣቶችን አለመስገድ ያዩ የንጉሱ ታማኞች ንጉሱ ዘንድ ሄደው ወጣቶቹን ታማኝነት በማጉደልና ሀገርን በመክዳት ወንጀል እንዲያቃጥላቻ ጠየቁ፤ ንጉሱም ላሰራው ምስል እንዲሰግዱ፣ እምቢ ካሉ ግን እቶን እሳት ውስጥ እንደሚጥሏቸው ቢያስጠነቅቃቸውም አንሰግድም ብለው ከአቋማቸው ሳይነቃነቁ ቀሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ይህ አምባገነን የነበረ ንጉስ የፈቀደውን የሚገድል፣ የሚያስር፣ የሚመታ እና የሚያዋርድ እንዲሁም ለእሱ ተገዥ የሆኑትን ደግሞ ከፍከፍ የሚያደርግ ነበርና እነዚህን ሶስት ወጣቶች ከዚያ ከሚቀለቀል እቶን እሳት ውስጥ ከተቷቸው፡፡
ኢህአዴግ እንደ ናቡከደነፆር
በአሁኑ ሰዓት ኢህአዴግ እየሰራ ያለው ይህንኑ የንጉስ የናቡከደነፆር አይነት ስራ ነው፡፡ በፈለገው ሰዓትና ቀን ህገ መንግስቱን ይሽራል፣ ይለውጣል፡ ፡ ማሰር መምታትና መግደል ካሰኘው ያደርገዋል፡፡ እሱ በሚጠራው ሰልፍና ስብሰባ ላይ በግዳጅ እያስወጣ ፓርቲው ህብረትና አንድነት እንዲሁም ሙሉ ኃይል ያለው ያስመስላል፡፡ በትምህርት ውጤታቸው የላቁ ልጆችን በየትምህርት ቤቱ እየዞረ አባል እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የ‹‹ኢህአዴግዝም››ንም እምነት ይከተሉ ዘንድ በወጣት ሊግና ፎርም አደረጃጀት ይጠይቋቸዋል፡፡ ከዚያም በየስብሰባው ሚሪንዳና ቦንቦሊኖ እያደለ በብሔር ብሔረሰቦች ዘፈን እያስጨፈረ ስለ ደርግ ጭፍጨፊነት እና ስለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጭራቅነት እየሰበካቸው እሱን እሱን ብቻ እንዲያመልኩ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚሁ የኢህአዴግዝም እምነት ጠንካራ አምላኪ ከሆንክ ደግሞ ያለ ውድድር ስራ መግባቱ፣ ሹመትና እድገቱ፣ ቤትና መኪናው፣ 10ኛ ክፍልን ሳትጨርስ አመራር ቦታ ላይ መቆሙ፣ በቃ ምን አለፋህ… ሁሉ በእጅህ ነው፡፡
ኢህአዴግ ከድሮው ንጉስ ናቡከደነፆር የሚለየው ሳይሰራ ሊያሰግድ የሚጥር ግትር መሆኑ ነው፡፡ ማሰገዱ በጎ ባይሆንም የድሮው ንጉስ ያሰግድ የነበረው ለህዝብ የሚታይ ነገርን ሰርቶ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ግን እንዲሰገድለት የሚፈልገው በማይታየው፣ በሌለውና ባልተሰራው ስራው ነው፡፡ በአጭሩ ያላዩት እንዲያምኑት የሚፈልግ የዘመኑ ነብይ ለመሆን ይሞክራል፡ ፡ ትራንስፎርሜሽን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስትና ሌሎችም…. የሚጨበጡ የሚያዙ አይደሉም፡፡ እነዚህ የማይጨበጡ ነገሮችን ግን ከምንም በላይ አጋንኖ ያቀርባቸዋል፡፡ በእነዚህ ስራዎች፣ ለእነዚህ ‹‹መሃንዲስ›› ለተባሉት ካድሬና መሪዎቹ እንድንሰግድለት ይጠብቃል፡፡
በአጠቃላይ ልክ በድሮ ዘመን የነበረው ናቡከደነፆር ያደርግ እንደነበረው ለኢህአዴግና ለመሪዎቹ ለሰገደ ሁሉ ከሚገባው በላይ ከአገርና ከህዝብ ጥቅም ይሰጠዋል፡፡ ይዘርፋል ማለት ይቀላል፡፡ ኢህአዴግ ሳይቀር ያወጣውን ህግ ጠቅሶ ‹‹መብቴ ነው!›› እያለ፣ ለመስገድ አሻፈረኝ ያለ ግን እንደ ሶስቱ ወጣቶች የዘመኑን የእሳት ነበልባል ይቀምሳል፡፡ ወደ እስር ቤት ይወረወራል፡፡ ይደበደባል፡፡ ከስራ ይባረራል፡፡
ወይንሸት ንጉሴ
ወይንሸት ንጉሴ
ነገር ግን አንተ እውነተኛው የኢትዮጵያ ልጅ ከራስህ ጥቅም ይልቅ የሀገርህን ጥቅም የምታስቀድም ከሆነ እና ከምግብ ይልቅ ነፃነት፣ ከብሔር ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን፣ ከውሸት ይልቅ እውነትን መርጠህ ይህን መንግስት ከተቃወምክ ወይም ከተቸህ የኢህአዴግ አምላኪዎች በገባህበት እየገቡ ዛቻና ማስፈራሪያ፣ ስድብና ዱላ መለያህ ያደርጉልሀል፡፡ ይህ ነገር ግን አቋምህን ሊያስቀይረው አለመቻሉን ሲያውቁ ደግሞ ደስ የምትል ውሸት አቀናብረው ፊልም ይሰሩ እና አሸባሪ፣ ከዳተኛ፣ የሀገር ጠላት ብለው ንጉስ ናቡከደነፆር እሳት ውስጥ እንደከተታቸው ሶስቱ ወጣቶች ሁሉ ኢህአዴግም ይወረውርሃል፡፡ ከደበርከውም ያስወግድሃል፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ዛሬም አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤልን የመሳሰሉ ወጣቶች እንዳሉ ያወቀ አልመሰለኝም፡፡
በእርግጥ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ወጣቱ ሀገራዊ ጉዳይ አያገባኝም ብሎ እርፍ ብሎ ቢታየውም ዛሬ ደግሞ እንደ አዲስ መታሰርም መደብደብም ሆነ መሞት የማይፈሩ፣ ባመኑበት እንጂ ለማያምኑበት ነገር የማይገዙና የማይንበረከኩ፣ ጥቅማ ጥቅም የማያታልላቸው፣ ለመብታቸው የሚታገሉ ለሀገራቸው ክብር የሚቆረቆሩ እና ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የሀገራቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ወጣቶች ማቆጥቆጥ ጀምረዋል፤ በቅለዋል፡፡ እናም ኢህአዴግ ሆይ! እንደ ንጉስ ናቡከደነፆር ከመሆንህ በፊት መንገድህን አስተካክል! (ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ)

ሕወሓት ከምርጫ 2007 በኋላ ጠቅላይ ሚ/ር ለመቀየር አስቧል – ሃይለማርያም ውጣ፤ ቴዎድሮስ ግባ?

ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም አቶ መለስን ለመምሰል ቢሞክሩም፤ በሕወሓቶች ዘንድ ግን ማስመሰላቸው ሊዋጥላቸው አልቻለም

በሃገር ቤት የሚታተመው አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው ገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በሙስና ስም የ“ማጥራት ዘመቻ” ማካሄዱን ተከትሎ በመንግሥት ሥልጣን ላይ በሚገኙ የፓርቲው አመራሮች መሐል ተከስቷል በተባለ አለመተማመንና መጠራጠር መስፈኑ ካድሬዎችን በእጀጉ እንዳስጨነቀ ተጠቆመ። ኢህአዴግን ለመሰናበት የሚፈልጉ በርካታ ካድሬዎች “ለምን” በሚል የሚቀርብላቸውን ጥያቄ ለመመለስ በመቸገራቸው ብቻ በፓርቲውን ውስጥ ለመቆየት መወሰናቸውንም ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልጸዋል።


ካድሬዎቹ ቀደም ሲል ኢህአዴግን ተሰናብተው ለወጡና በተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው በማገልገል ላይ ለሚገኙ የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው “በደህና ጊዜ ተገላገልክ” በሚል በፓርቲው ውስጥ ችግር ስለመኖሩ እየነገሯቸው መሆኑን የጠቀሰት የዜና ምንጮቹ፣ ለስራ ከሃገር መውጣት የማይችሉ ባለስልጣናት ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ። ለሃላፊዎቹ ደህንነት ሲባል የሚሰሩበትን ተቋምና ስም መናገር እንደማይችሉ በመጥቀስ መረጃውን የሰጡት ክፍሎች “ባለስልጣኖቹ በመካከላቸው እርስ በርስ መተማመን በመጥፋቱ ችግራቸውን መወያየት እንኳን አይችሉም” ብለዋል፡፡
“በጣም የሚቀርቡኝ ጓደኞቼ ገንዘብ ወደ ውጪ እንድወስድላቸው እስከመጠየቅ ደርሰዋል” ሲሉ የገለጹት አነድ የቀድሞ የኢህአዴግ ባለስልጣን፣ ፓርቲው በሙስና ስም ያካሄደው የሽግግር ወቅት የማጥራት ርምጃ የፈጠረው ስሜት አሁን ድረስ እንዳለ ጠቁመዋል። ሰሞኑንን ወደ አሜሪካ ያቀኑ
የቀድሞ የኢህአዴግ አመራር “ኢህአዴግ በከፍተኛ የመበስበስ አደጋ ውስጥ ይገኛል። በዚህም የተነሳ ካድሬው ተዥጎርጉሯል” ሲሉ መናገራቸውም
ተገልጿል።
ይሕ በእንዲሕ እንዳለ የየኢሕአዴግ አባል ድርጅት የሆነው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሐት) ከምርጫ 2007 በኋላ ለሁለት ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙትን ኃይለማርያም ደሳለኝን በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም ለመተካት እንቅስቃሴ መጀመራቸው በፓርቲው ውስጥ
ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ሪፖርት መቅረቡ ተሰምቷል። ይኽው ሪፖርት የቀረበላቸው ክፍሎች ቀደም ሲል እንዳደረጉት የህወሐትን ከፍተኛ አመራሮች በማነጋገር እየወተወቱ (ሎቢ እያደረጉ) መሆናቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮቹ ተናግረዋል።


ምንጭ አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ (በሃገር ቤት የሚታተም)

Monday, April 7, 2014

ኖርዌይ ኢህአዴግ ያሰረባትን ዜጋዋን ጉዳይ እየተከታተለች ነው ።

ኖርዌይ ኢህአዴግ ያሰረባትን ዜጋዋን ጉዳይ እየተከታተለች ነው

ማዕከላዊ እስርቤት ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸዋል በሚል ተሰግቷል

የኢህአዴግን ካዝና የምትሞላዋ ኖርዌይ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙትን ዜጋዋን አስመልክቶ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየሰራች መሆንዋ ታወቀ። በማዕከላዊ እስር ቤት የታሰሩት ዜጋዋ ድብደባና ቶርቸር እንዳይካሄድባቸው በቅርብ ክትትል እያደረገች መሆንዋን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ክፍሎች ለጎልጉል አስታውቀዋል።
ኢህአዴግን ከልጅነቱ ጀምራ ስትደጉም የኖረቸውና አሁን ደግሞ “በልማታዊ መንግሥትነት” መድባ ድጋፏን የምትዘረጋለት ኖርዌይ ዜጋዋን አስመልክቶ አስፈላጊውን ሁሉ የማድረግ ግዴታ እንዳለባት ይታወቃል። በዚሁ መሰረት የኖርዌይ ትልቁ ጋዜጣ ቀደም ሲል ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ ይፋ ያደረገውን ዜና የሚያረጋግጥ ዜና አሰራጭቷል።
ደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሃይሎች አሳልፈው ለኢህአዴግ የሰጧቸው የቀድሞ የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦኬሎ አኳይ የኖርዌይ ዜግነት እንዳለቸው በማረጋገጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተለው፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲም ስራውን እየሰራ እንደሆነ አፍተን ፖስት አመልክቷል።
አፍተን ፖስት “የሰብአዊ መብት ተከራካሪ” ሲል በዜናው መክፈቻ የጠቀሳቸውን አቶ ኦኬሎ አኳይን አስመልክቶ የውጪጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን አማካሪ ስቫይን ሚኬልሰንን ጠቅሶ “አቶ ኦኬሎ የደቡብ ሱዳን የደህንነት ሃይሎች በደቡብ ሱዳንና በዩጋንዳ ድንበር መካከል ይዘዋቸዋል። አንደተያዙም ወደ ጁባ ሳይወሰዱ ተላልፈው ተሰጥተዋል” በማለት የጉዳዩን አካሄድ አመላክቷል።
የኢህአዴግን የገቢ ምንጭ የሆነችው ኖርዌይ በጉዳዩ አቋም በመያዝ ያስታወቀችው ስለመኖሩ ዜናውን የዘገበው አፍተን ፖስት ያለው ነገር የለም። ይሁን አንጂ ድርጊቱን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ኖርዌይ እንደምትቃወመው አልሸሸገም። አቶ አኳይ ለምን ወደ ስፍራው እንደተጓዙ በውል የተገለጸ ነገር እንደሌለ ዜናው ጠቁሟል። “በተመሳሳይ” በማለት ከዜናው ግርጌ ኢህአዴግ ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት ክብር እንደሌለው፣ በነጻ ፕሬስና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እያደር የከረረ ርምጃ በመውሰዱ ክፉኛ የሚዘለፍበት ጉዳይ እንደሆነ አጣቅሷል።
ጎልጉል መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓም (March 28, 2014) ቀን ዜናውን ይፋ በማውጣት ቅድሚያ ወስዶ ሲዘገብ አቶ ኦኬሎ ከደቡብ ሱዳን ከሆቴል ውስጥ ታፍነው መወሰዳቸውን ጠቁመን ነበር። አሁን አዲስ በመጣው መረጃ በዩጋንዳና በደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ ተያዙ መባሉ ምን አልባትም ኢህአዴግ ሊመሰርትባቸው ላሰበው ክስ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ እንደሚሆን ጥርጣሬ አለ። የዜናው ምንጭ አቶ ኦኬሎ ከጁባ በሄሊኮፕትር መወሰዳቸውን እንደሚያውቁ ገልጸዋል።
በመለስ ዜናዊ ውሳኔና ትዕዛዝ በአኙዋክ ተወላጆች ላይ በጅምላ የተከናወነውን ጭፍጨፋ አስመልከቶ ተቃውሞ በማሰማት፣ አድርጉ ተብለው የታዘዙትን ባለመቀበል አገር ጥለው የኮበለሉት አቶ ኦኬሎ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያገባናል በሚሉ “አክቲቪስቶች”፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና፣ ማህበራት ዘንድ ዋንኛ ርዕስ ያለመሆናቸው ምክንያት አስገራሚ እንደሆነባቸው የሚጠቁሙ ዲያስፖራዎች ጥቂት አይደሉም። ከዚያም አልፎ አሁንም የመታሰራቸው እና እርሳቸውን ለማስፈታት በሚደረገው ሁኔታ ላይ የተፈጠረው ዝምታ አጠያያቂ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
አቶ ኦኬሎ ማዕከላዊ እስር ቤት እንደሚገኙና፣ በዚያም በከፍተኛ ደረጃ ቶርቸር ይደረጋሉ በሚል ስጋት ሁኔታውን ለሚመለከታቸው በማሳወቅ በኩል አንዳንድ ወገኖች እንቅስቃሴ መጀመራቸው ታውቋል። ኢህአዴግ እስካሁን ፍርድ ቤት ያላቀረባቸው አቶ ኦኬሎ “አሁን ስለሚገኙበት የጤና ሁኔታ የኖርዌይ ኤምባሲ የጉብኝት ሪፖርትና ይጠበቃል” ሲሉ እኚሁ ክፍሎች አመላክተዋል።
ከቤተሰባቸው ተነጥለው በስደት ከሚኖሩበት ኖርዌይ ወደ ደቡብ ሱዳን ያመሩት የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ደቡብ ሱዳን በህወሃት ሙሉ ቁጥጥርና ፈቃድ የምትንቀሳቀስ አገር መሆኗን እያወቁ ወደዚያ ማቅናታቸውን “ታላቅ ጥፋት” መባሉን መዘገባችን ይታወሳል። ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አሁንም አልተሳካም። ባምቤላ የአኙዋኮች ጭፍጨፋ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ኦሞት ኦባንግ በቅርቡ መኮብለላቸውና በብዙዎች ዘንድ አውሮጳ እንዳሉ ቢነገርም በትክክል ያሉበት አገር በይፋ አለመታወቁን መዘገባችን አይዘነጋም።

አገራችን ምን አይነት ምስቅልቅል ውስጥ እንደሆነች ለማንም ማስረዳት አስፈላጊ አይደለም።

በዋሽንግተን ዲሲ የሽግግር ምክርቤቱ አመራርm ስብሰባ

ውድ ኢትዮጵያውያን፤

አገራችን ምን አይነት ምስቅልቅል ውስጥ እንደሆነች ለማንም ማስረዳት አስፈላጊ አይደለም። ከዚህም አልፎ ተዘጋጅተንና አቅደን ካልጠበቅነው መጭው ስርአት ተመሳሳይ ወይም ከዚህኛው የከፋ ይሆናል ብለን ሁላችንም እንሰጋለን። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት ይህንን የዝግጅት አስፈላጊነትን ጽንሰ ሀሳብ ለህዝብ በአንክሮ ካስገነዘበ ወዲህ ዛሬ ይህ አጀንዳ በተቃዋሚ ድርጅቶች፤ በተለያዩ ተቋማት እንዲሁም በመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የመወያያ ርእስ ሆኗል።  

በመጭው እሁድ ሚያዝያ 5 (April 13, 2014) ባዘጋጀነው ስብሰባ የተለያዩ የማህብረሰባችን ተወካዮች በዚሁ አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ንግግር ያደርጋሉ ከህዝብም ጋር ይወያያሉ። ይህ ስብሰባ የተሳካ ለማድረግ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የሚገኙ ጓደኞችዎንና ዘመድ ወዳጆችዎን በመጋበዝና እራስዎም በመገኘት የድርሻዎን ያበርክቱ ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን። ስለስብሰባው በይበልጥ ለማወቅ፤ ከዚህ ኢሜይል ጋር ተያያዥ ሆኖ የተላከውን በራሪ

ወረቀት ይመልከቱ።

የሽግግር ምክርቤቱ አመራር

Wednesday, April 2, 2014

ኢሳት የኔ ነው በትሮንዳይም...!!!



ኢሳት የኔ ነው በሚል ዝግጅት በኖርዌ ዓገር  በትሮንዳይም ከተማ ዓገር ወዳድ በሆኑት ኢትዮጽያዊያን የተዘጋጀው ዝግጅት ድባቡ ይሄንን ይመስል ነበር።
http://ethsat.com/video/esat-yene-new-norway-throndheim/