Saturday, April 26, 2014

ዝምታችን ይበቃል......!!!!


<< ቀለል ብሎ ከበድ ያለ ጥያቄ፡- ከእኔ ምን ይጠበቃል!? >>
በሀገራችን ኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ በኃይል የተጫነው እራሱን "መንግሥት" ብሎ የሚጠራው ሕወሓት/ኢህአዴግ፤ ለ"ሀገር"/ድርጅት ደህንነት፣ መከላከያ እንዲሁም ፖሊስ በሚሰጠው የቀጥታ ትዕዛዝ እነሆ አማራጭ መንገድ አለን የሚሉ የፖለቲካ አመራርና አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም ንፁሐን ዜጎችን አስከፊውን የቀይ ሽብር እንዲሁም በጀርመን የናዚን ዘመን በሚያስታውስ ሁኔታ ከየመንገዱ እና ከየቤታቸው ከሕግ በላይ ሆኖ በማፈስ ወደ ከርቸሌ እንዲሁም ወዳልታወቀ ቦታ እየወሰዱ ድብደባ፣ ወሲባዊ ትንኮሳ እና አካላዊ ሥቃይ በማድረስ ላይ መሆናቸው ያደባባይ ምሥጢር ነው።
አንድ የውጭ ወራሪ ኃይል እንኳን በወረረው ዜጋ ላይ ሊያደርሰው የማይችለውን ዓይነት ውርደት እና ሥቃይ በሙስናና በሞራል ዝቅጠት የላሸቀው የሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በገዛ ዜጎቹ ላይ (የከፍተኛ አመራሮች ዜግነት ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ሆኖ) እያደረሰ መገኘቱን ይህ ትውልድ እንዴት እንቀበለዋለን? ምንስ እናደርጋለን?
እነሆ እስከዛሬ ድረስ ሕወሓት ሕግ አውጪ፣ ዳኛ፣ እንዲሁም ፖሊስ በሆነባቸው ተቋማት አማካኝነት አሸባሪ ተብለው እስር ቤት የሚማቅቁ ዓለም እልል ብሎ የሸለማቸው ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ የፖለቲካ አመራሮችና አባላትን ጨምሮ ሰሞኑን በገፍ እየተጋዙ ያሉትን ቆራጥ፣ ወጣት-የነብር-ጣት ወንድሞች እና እህቶች ሕወሓት 23 ዓመት ሙሉ ለመሸርሸር ወጥሮ የደከመበትንና የኢትዮጵያችንን እንዲሁም የዜጎችን መብት፣ አንድነት እና ክብር ለማስመለስ መሥዋዕትነት እና ዋጋ እየከፈሉ ነው።
አሁንም ጊዜው በጣም አልረፈደም፣ ዝምታችን ይበቃል። ጎጂ ባህል የሆነውን ወደሌሎች ጣታችንን መቀሰር፣ እንዲሁም ስህተት ቢሰሩም እንኳን ከዚህ ቀደም ሠርተው የወደቁትን (ያልተሳካላቸውን) እንዲሁም እየሠሩ ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች፣ ግለሰቦች በተደጋጋሚ መተቸት የሰነፍ ቀዳሚ መለያና አጉል ምክንያት መሆኑን ተገንዝበን፤ "ከእኔ ምን ይጠበቃል?" ብለን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የምንችለውን ጠጠር ለመወርወር ቆርጠን መነሳት ያለብን ትላንት ቢሆንም ቅሉ፤ አሁንም ግን ዕድሉ አለና ይበቃል እንበል። ዛሬ ግን የመጨረሻው ይመስላል።
የምንችለውን ሁሉ በማድረግ፡-
>> ይህን አስከፊ የሕወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት ከኢትዮጵያችን ጫንቃ እናላቅቅ፣
>> ግፈኞቹን በሕግ ፊት እናቅርብ፣
>> ከሁሉ ጠቃሚ የሆነውን በሀገራችን ብሔራዊ ዕርቅ እንዲካሄድ እንስራ፣
>> ይዘታቸው ወደ ሕወሓት የግል ንብረትነት የተቀየረውን የመንግሥት (የሕዝብ) ተቋማት እንደኛ ለመመሥረት አስተዋፅዖ እናበርክት ወዘተርፈ...
ጎበዝ፤ ይህን ሁሉ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በተደራጀ መልኩ ብቻ በመሆኑ፤ ለውጥ አመጣለሁ ብለን በምናምንበት ማንኛውም አማራጭ የፖለቲካ ኃይል፣ የዴሞክራሲ ግንባታ ተቋም፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅት፣ የማኅበረሰባዊ ድርጅት ውስጥ ወዘተርፈ . . . በመሳተፍ ጠብ የሚል ነገር እናምጣ።
ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች፣ ወደልጆችዋም ጭምር!
ከክብሩ ደመቀ

No comments:

Post a Comment