Tuesday, September 30, 2014

ኢትዮጵያውያኑ ላይ የተኮሰው የኤምባሲው ታጣቂ ታሰረ!!!

”መሣርያውን ወደሚከራከሩት ሰዎች ደገነ እና ተኮሰ” ”He points the weapon at others who argue with him and fires” ሮይተርስ ከዋሽግተን ዲሲ ዛሬ የዘገበው።

ዛሬ መስከረም 19፣2007 ዓም ዋሽግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተቃዋሚ ኢትዮጵያውያን ቁጥጥር ስር ውሎ ባለ ኮከቡ ሰንደቅ ዓላማ በነፃው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተቀይሯል። ተቃውሞውን አስመልክቶ ኢሳት ዘግይቶ በለቀቀው ተጨማሪ ዘገባ ተቃዋሚዎቹ በኢምባሲው ውስጥ ዘልቀው የአቶ አንዳርጋቸውን እና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ”ነፃነት! ነፃነት!” ሲሉ አሳይቷል።


ቀደም ብሎ አምባሳደር ግርማ ብሩ በሸሚዝ እንደሆኑ ከሌሎቹ የኢምባሲው ሰራተኞች ጋር ቆመው ሲመለክቱም ሌላው የታየው ትዕይንት ነበር።ተቃውሞውን ተከትሎ የዓለም ስመጥር የዜና አገልግሎት ድርጅቶች ሮይተርስ እና የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ኤ ኤፍ ፒን ጨምሮ የቪድዮ ምንጫቸው ኢሳት የኢትዮጵያውያን ቴሌቭዥን መሆኑን ከመጥቀሳቸውም በላይ የኢሳትን ሰበር ዜና የያዘ ቪድዮ በቀጥታ ለጥፈው ታይተዋል።በመሆኑም በዛሬው እለት ኢሳት በመላው ዓለም የዜና አውታሮች የመወሳቱን ያህል ከእዚህ በፊት በእዚህ አይነት ስፋት በመላው ዓለም በሚገኙ ታላላቅ የዜና አውታሮች የተጠቀሰ አይመስለኝም።

በሌላ በኩል በአሜሪካን ሕግ ሽጉጥ ተኩሶ ማስፈራራት አይደለም በአንደበቱ ለማስፈራራት የሞከረ የሚደርስበት ቅጣት ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል።ሆኖም ግን የኢምባሲው ሰራተኛ በተኮሰው ጥይት አካባቢውን በማሸበር እና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ባሰሙ ዜጎችን በማስፈራራት ሕግ መጣሱን ለማወቅ ተችሏል።በአሁኑ ሰዓት ግን ግለሰቡ በቁጥጥር ስር መሆኑን በርካታ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች እየጠቀሱ ይገኛሉ።ሆኖም ግን ግለሰቡ የዲፕሎማቲክ ከለላ ካለው አሜሪካ በአጭር ጊዜ ከሀገር እንዲወጣ ልታደርግ ትችላለች።በመሆኑም NBC የዜና አገልግሎት የተኮሰው የኢምባሲ ሰራተኛ መታሰሩን ገልጧል።

ጉዳዩን ተከትሎ በነገው እለት ከኢትዮጵያ የሚወጣው መግለጫ ይዘት ከወዲሁ መገመት አያስቸግርም። ሆኖም ግን ምንም አይነት መግለጫ እና ማብራርያ ቢሰጥ በአሜሪካውያንም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ፅንሰ ሃሳብ አንፃር ከጠቅላላ ጉዳዩ ውስጥ የኢምባሲ ሰራተኛው ምንም አይነት የጦር መሳርያ ባልያዙ በባዶ እጃቸው ተቃውሞ ባሰሙ ኢትዮጵያውያን ላይ የጦር መሳርያ በመደገን የማስፈራራቱ እና በኃላም የመተኮሱን ያህል የጎላ እና አናዳጅ ነገር ነጥሮ አይወጣም። በመሰረቱ ዜጎች የሀገራቸውን ኢምባሲ ሲቃወሙ ይህ አዲስ አይደለም።እራሷ አሜሪካ የእራሷ ዜጎች ባልሆኑ ግን በሌሎች ሀገሮች ዜጎች ኤምባሲዋ ተውሯል።

በዲፕሎማሲው ዓለም ደግሞ አንድ ኢምባሲ በራሱ ሀገር ተወላጆች በተቃውሞ ቢናጥ ጉዳዩ የዓለም ዓቀፉን የቬና ስምምነት ከመመልከት ይልቅ የአንዲት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ገንፍሎ የመውጣት አይነተኛ አመላካች ጉዳይ ከመሆን አያልፍም።ከእዚህ በዘለለ ኢምባሲው ጉዳዩን ለፖሊስ ደውሎ እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ አራት ኪሎ ያለ ይመስል ዋሽግተንን በተኩስ መናጡ ነው አሜሪካኖችን የሚያናድደው።

በመጨረሻም አንድ ነገር ማንሳት ይቻላል።ባራክ ኦባማ ከአቶ ኃይለማርያም እና ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ቁጭ ብለው ካወሩ ገና ሳምንት ሊሆነው ነው።የዛሬው በመዲናቸው ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቃውሞ ያሰሙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ለኦባማም ጭምር የሚያስደነግጥ ነው። የኦባማ የአፍሪካ ፖሊሲ ዕውን በጥናት ላይ የተመሰረተ ነው? ላለመሆኑ ማሳያው የዛሬው 
ጠንካራ ተቃውሞ ነዋ!

Saturday, September 27, 2014

መስቀልን በቃሊቲ

የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችና የነገረ ኢትዮጵያ የዝግጅት ክፍል ባልደረባ መስከረም 18/2007 ዓ.ም (መስቀልን) ቃሊቲ ከሚገኙ ታሳሪዎች ጋር አሳልፈዋል፡፡ በወቅቱም አቶ በቀለ ገርባን፣ አቶ ኦልባና ሌሊሳን፣ አዛውንቱን ሲሳይ ብርሌን፣ አቶ ጉታ ዋቆንና ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን አግኝተዋል፡፡ ነገረ ኢትዮጵያ ከታሰሪዎቹ መካከል የተወሰኑትን መልዕክት እንደሚከተለው አቅርባለች፡፡ 

‹‹ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ተጠናክረው የብሄር ፓርቲዎችን ማጥፋት አለባቸው›› አቶ በቀለ ገርባ
ከዝዋይ ወደ ቃሊቲ ከመጣሁ 11 ወራት ሆኖኛል፡፡ በህዳር ወር 2006 ዓ.ም ነው ወደ ቃሊቲ የመጣሁት፡፡ በአሞክሮዬ መሰረት ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም መፈታት ቢገባኝም አሁንም ድረስ እስር ቤት ውስጥ እገኛለሁ፡፡ በወቅቱ በአሞክሮዬ መሰረት መፈታት እንዳለብኝ ለእስር ቤቱ ኃላፊዎች ደብዳቤ ጽፌ ነበር፡፡ ሊፉቱ ሲፈልጉ አስጠርተው ያነጋግሩሃል፡፡ ካልፈለጉ ደግሞ ዝም ይሉሃል፡፡ እኔ ደብዳቤ ብጽፍም አልተጠራሁም፡፡ ምክንያታቸውን ባላውቅም ሊፈቱኝ አልፈለጉም ማለት ነው፡፡ ግን በአሞክሮዬ ባለመፈታቴ አልተጎዳሁም፡፡ በርካታ ነገሮችን ተምሬበታለሁ፡፡ እንዲያውም የሚጎዱት እነሱው ራሳቸው ናቸው፡፡ በርካታ ታሳሪዎች አሳሪዎቹ ለቃላቸውም ሆነ በህጉ ተገዥ እንዳልሆኑ በእኔ ጉዳይ ተምረዋል፡፡ አሁን በመጋቢት ወር ዋናውን ፍርድ ጨርሼ እፈታለሁ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡

እኔ የማምነው በባለሙያነቴ ነው፡፡ ፖለቲከኛ ነኝ ብዬ አላምንም፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን እንደ ግለሰብ ፍትህን እሻለሁ፡፡ ስልጣን ላይ ማንም ይምጣ ማን ፍትህን የሚሰጥ ከሆነ ችግር የለብኝም፡፡ በሙያተኝነቴ ነው መቀጠል የምፈልገው፡፡ ነገር ግን ክፍቶች አሉ፡፡ ወደ ፖለቲካው የገባሁትም ክፍተቶችን በማየቴ ነው፡፡

ህብረ ብሄራዊ የሚባሉ ፓርቲዎች ለአብዛኛው ህዝብ ተደራሽ አይደሉም፡፡ የህብረ ብሄር ፓርቲዎች ድክመት ደግሞ የብሄር ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በእነሱ መዳከም ነው የብሄር ፓርቲዎች በየ ቦታው ለመመስረት እድል የሚያገኙት፡፡ ህብረ ብሄር ፓርቲዎች የአንድን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት አቅም የላቸውም ብሎ ያሰበ አካል/ሰው እወክለዋለሁ በሚለው ማህበረሰብ ስም ፓርቲ ያቋቁማል፡፡ እኔም በዚህ ክፍተት ነው ወደ ፖለቲካው የገባሁት፡፡ ይህ ችግር ባይኖር ማህበረሰብን ከፋፍሎ ‹‹ይህኛው ፓርቲ የዚህ፣ ያንኛው ደግሞ የዚህኛው ማህበረሰብ ፓርቲ ነው›› ተብሎ እንዲከፋፈል ፍላጎት የለኝም፡፡

ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች ቢጠናከሩ በአንድነት መታገልን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ከአንዱ ዓለም አራጌ ጋር በታሰርንበት ወቅት ‹‹እናንተ ከተጠናከራችሁ እኛ እንጠፋለን፡፡ እናንተ ተጠናክራችሁ በብሄር የተደራጀነውን ማጥፋት አለባችሁ፡፡ ተጠናከሩና እኛን አጥፉን፡፡ ያኔ ሁላችንም በአንድነት እንታገላለን፡፡ ችግሮችም ይፈታሉ›› እለው ነበር፡፡ የህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች አለመጠናከር እንጅ ለዚህኛው አሊያም ለዛኛው ህዝብ ብዬ መስራት አልፈልግም፡፡ በአንድነት መስራትን የመሰለ ነገር የለም፡፡

ህብረ ብሄር ፓርቲዎች በአንድ በኩል በመረጃ እጥረት፣ በሌላ በኩል በስህተት፣ አሊያም አይቶ በማለፍ የአንድን ማህበረሰብ ችግር ችላ ይሉታል፡፡ ይህ ነው ተነጣጥሎ ለመታገል፣ ለብሄር ፓርቲዎች መበራከት ምክንያት የሆነው፡፡ ህዝብ መብቱ እስከተከበረለት ድረስ ማን መጣ ማን ትኩረት አይሰጥም፡፡ ህብረ ብሄር ፓርቲዎች መዳከም ግን የብሄር ፓርቲዎች ተደማጭነት እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል፡፡ አሜሪካን ለምሳሌ ብንወስድ ህዝቡ መብቱ እስከተከበረለት ድረስ ጥቁር መራ ነጭ ችግር የለበትም፡፡ የእኛ አገርም ጉዳይ ተመሳሳይ መሆን ይችላል፡፡ በዚህ ላይ እኛ ወንድማማቾች ነኝ፡፡

እኔ ህብረ ብሄር ፓርቲዎችን እወቅሳለሁ፡፡ እነሱ ከተጠናከሩ በየቦታው በተናጠል የሚደረገው ትግል ወደ አንድ ጠንካራ ትግል ይመጣል፡፡ እነሱ ከተጠናከሩ በተናጠል የሚደረገው ጭቆና ይቀንሳል፡፡ ክፍተት ባይኖርና ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ለሁሉም ህዝብ መድረስ ቢችሉ እኔ በሙያዬ በቀጠልኩ ነበር፡፡ እንዲህ የምንታሰረውም እኩ ከድክመታችን የተነሳ ነው፡፡ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ቢኖረን እኮ እኛም አንተሰርም ነበር፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የአገራችንን ችግር መፍታት አንችልም፡፡ በተናጠል ለጭቆና እንዳረጋለን፡፡ በተናጠል እንታሰራለን፡፡ በሂደት ጭቆናውን እየለመድነው እንሄዳለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ጭንቅ ላይ እንዳለች እርጉዝ ሴት ነች›› አቶ ሲሳይ ብርሌ

የተፈረደብኝ 13 አመት ነው፡፡ ከታሰርኩ አራት አመት ሆኖኗል፡፡ እድሜየ 65 ደርሷል፡፡ እስር ቤት ውስጥ ችግር አለ፡፡ የእስር ቤቱን ኃላፊዎች የምናገኛቸው ህክምና ስንፈልግ ነው፡፡ ነገር ግን የህክምናው ጉዳይ ባይወራ ይሻላል፡፡ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ ውጭ ያለው ህዝብም በሰፊው እስር ቤት ውስጥ እንዳለ ነው የሚቆጠረው፡፡ ልዩነቱ የተሻለ ነፋስ ስለምታገኙ፣ ስለምትዘዋወሩና የፈለጋችሁትን ሰውም ስለምታገኙ ነው፡፡

እኛ እያረጀን ነው፡፡ ከእድሜያችን አንጻር በትግሉ ሂደት ብዙም የምንጨምረው ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ እናንተ ወጣቶች ናችሁ፡፡ ለትግሉ መሰረት የምትጥሉበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ወጣትነት ለትግል ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ አባት ያላወረሰውን ልጅ ሊያስቀጥል አይችልም፡፡ እናንተ አሁን ለራሳችሁ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችሁም ጭምር ነው የምትታገሉት፡፡ እናንተ በርትታችሁ ካልታገላችሁ ልጆቻችሁ ምንም የሚወርሱት ነገር አይኖርም፡፡ አባት ያላወረሰውን ደግሞ ልጅ ምንም ነገር ሊያስቀጥል አይችልም፡፡ በመሆኑም እናንተ ከአሁኑ ለእውነት በመቆም ልጆቻችሁ የሚያስቀጥሉት ነገር መስራት አለባችሁ፡፡

ጭቆና እስካለ ድረስ እኔም ሆንኩ እናንተ ባንታገልም ጭቆናውን ለማስወገድ የሚነሳ ሰው አይጠፋም፡፡ እናንተን እድለኛ የሚያደርጋችሁ ጭቆናውን ለመግታት ፈልጋችሁ፣ በራሳችሁ ተነሳሸነት በመጀመራችሁ ነው፡፡
ጭንቅ ላይ ያለች እርጉዝ ሴት ካላማጠች አትገላገልም፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያ ጭንቅ ላይ እንዳለች እርጉዝ ሴት ነች፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ከሚደርስባት ስቃይ ለመገላገል ማማጥ አለባት፡፡ ያኔ ትገላገለዋለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ትግል ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች መታገል አለባችሁ፡፡ ትግሉ ጥንካሬን ይጠይቃል፡፡ መጠንከር አለባችሁ፡፡

‹‹ተቃዋሚዎች በምርጫው ካላመኑበት ሁላችንም አንገባም ማለት አለባቸው›› አቶ ኦልባና ሌሊሳ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ምርጫው ቀድመው መስራት አለባቸው፡፡ ምርጫ ስለመግባት አለመግባት ከመወሰናቸው በፊት ጠንክረው መስራት ይገባቸዋል፡፡ ውሳኔውን ከመወሰናቸው በፊት ውሳኔውን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ነገር ማሰብ አለባቸው፡፡ ይህ ጉዳይ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ለውሳኔያቸው ደግሞ ተገዥዎች መሆን አለባቸው፡፡ አንዴ ከተወሰነ በኋላ ጠንካራ አቋም መያዝ አለበት፡፡ በህዝቡ አመኔታ ለማግኘት በውሳኔያቸው መጽናት አለባቸው፡፡ መወላወል አይገባም፡፡ ጊዜው እስኪደርስ ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡ በአንድ ወቅት 33 የሚባል ስብስብ ነበር፡፡ አሁንም ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለምርጫው በጋራ መስራት ያስፈልጋል፡፡

ተቃዋሚዎች በምርጫው መሳተፍ ለህዝብ የማይጠቅም መሆኑን ካመኑ እና መግባት የማያስፈልጋቸው ከሆነ በአንድነት ኃይልን አሰባስቦ ከምርጫው መውጣት ይቻላል፡፡ በምርጫው ካላመኑበት ሁላችንም አንገባም ነው ማለት ያለባቸው፡፡ በተናጠል ከምርጫው ራስን ማግለል ጥቅም አይኖረውም፡፡ በእርግጥ ይህ መወሰን ያለበት ጊዜው ሲደርስ ነው፡፡ እስከዛ ግን ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡
መጥታችሁ ስለጠየቃችሁን በጣም እናመሰግናለን፡፡ ውጭ ያለውን የቤት ስራችሁንም ጠንክራችሁ መስራት አለባችሁ፡፡

ነገረ ኢትዮጵያ በቀጣይ ጊዜያትም እስር ቤት ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ኢትዮጵያውያን መልዕክት ለማቅረብ ትጥራለች፡፡

Friday, September 26, 2014

የቴዎድሮስ ታደሰ እና የጃኪ ጎሲ ፍጥጫ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ መድረክ ጀርባ፤ ጃኪ ቴዎድሮስ ታደሰን ለምን ማጣጣል አስፈለገው?

ስለ ጃኪ ጎሲ ኮንሰርት ውዝግብ
ይህ የቁም ነገር መፅሔት ቅ ፅ 13 ቁጥር 187 ወሬ ልንገርህ ዕምድ ነው
መቼም አንድም አልበም ሳያወጣ በነጠላ ዜማዎቹ ብቻ የሚሊዮኖችን የሙዚቃ አፍቃሪያንን ልብ ስለተቆጣጠረው ጃኪ ጎሲ አላውቅም አትለኝም! ጃኪ ጎሲ ማነው? በእርግጥ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ጃኪ ጆሲ አይደለም፡፡ የመዝገብ ስሙ ጎሳዬ ቀለሙ ነው፡፡ ራሱ ነው ስሙን አሳጥሮ ጃኪ ጎሲ ያለው፡፡
እናስ? እናማ ባለፈው ሳምንት ለአዲሱ 2007 መግቢያ በከተማችን ከተዘጋጁት የሙዚቃ ኮንሰርቶች መካከል አንዱ የዚህ ወጣት ድምፃዊ ጃኪ ጎሲ ነበር፡፡ ታዲያልህ ለዚህ ዘመነኛ ወጣት ገና አንድ አልበም ሳያወጣ የተከፈለው ክፍያ ስንት እንደሆነ ሰምተሃል?ማን ነግሮኝ? በል ከተማው ውስጥ የለህም ማለት ነው፡፡ ለማንኛውም ለዚህ የመጀመሪያ ኮንሰርቱ 1.5 ሚሊዮን ብር እንደተከፈለው ይነገራል፡፡ ያው ክፍያው ቫትን ያካት አያካት ግልፅ አይደለም፡፡


እናስ? ጳግሜ 5 ምሽት በሚሊኒየም አዳራሽ ኮንሰርቱን ለማሳየት ቀጠሮ የተያዘለት ጃኪ ጎሲ ብቻ አልነበረም፡፡ ደግሞ ማን አለ አልክ? ሁለቱ አንጋፋ አርቲስቶችም ጃኪ ጎሲን እንዲያሯሩጡ ተጋብዘው ነበር፡፡ ማንና ማን መሰሉህ? አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴና ሌላው አንጋፋ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ ነበሩ፡፡
በፕሮግራሙ ቅደም ተከተል መሰረት አለማየሁ እሸቴ መጀመሪያ ገብቶ ከዘፈነ በኋላ ቴዎድሮስ፤ ከዚያ ጃኪ ጎሲና ቴዲ እየተፈራረቁ እንዲዘፍኑ ነበር እቅዱ፡፡ እናስ? እናማ በፕሮግራሙ መሠረት አለማየሁ ከአራት በላይ ዘፈኖቹን /ተማር ልጄን ጨምሮ/ ከተጫወተ በኋላ በዛው ዕለትና ሰዓት በካፒታል ሆቴል ሌላ መድረክ ስለነበረው ሹልክ ብሎ አመለጠ፡፡
ከዚያስ? ከዚያማ ያው ቴዎድሮስና ጃኪ መድረኩን በየተራ በመውጣት ተመልካቹን ካዝናኑ በኋላ የተመስገን ልጆች መድረኩን ተረከቡ፡፡ የተሜ ልጆች ለሁለት ዘፈን መድረክ ላይ ወጥተው አርባ አምስት ደቂቃ ሲቆዩ ሰዓቱ ወደ ስምንት ሰዓት ተኩል ደርሶ ነበር፡፡ በዚህ መሀል ውዝግብ ተጀመረ፡፡ በማንና በማን? በጃኪና በቴዎድሮስ ታደሰ ማናጀሮች መካከል፡፡ ለምን መሰለህ? የተመስገን ልጆች ከመድረክ ሲወርዱ መጀመሪያ መውጣት ያለብኝ ‹እኔ ነኝ – እኔ ነኝ› በሚል ማለት ነው፡፡
ለምን መሰለህ? የኮንሰርቱ ማብቂያ ሰዓት እየተጠናቀቀ ስለነበር ጃኪ ከወጣ በኋላ ከመድረክ ሲወርድ ተመልካቹ ወደ ቤቱ ስለሚሄድ መጀመሪያ መውጣት ያለብኝ እኔ ነኝ ያለው ቴዲ ነበር አሉ፡፡ በዚህ የመድረክ ጀርባ ውዝግብ ሲካሄድ የተመስገን ልጆች ውዝዋዜያቸውን ጨርሰው ወደ መድረክ ጀርባ ተመልሰው ነበር፡፡ ውዝግቡ በሁለቱ አርቲስቶች ማናጀሮች መካከል ለተወሰነ ደቂቃ ከተካሄደ በኋላ የቴዎድሮስ ታደሰ ማናጀር ባለቤቱ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰች፡፡
ውሳኔው ምን ቢሆን ጥሩ ነው? መጀመሪያ ጃኪ ጎሲ እንዲዘፍን ከተደረገ ቴዲ ከእሱ በኋላ አይዘፍንም አለች፡፡ እናስ? እናማ ጃኪ ጎሲ በዛየን ባንድ አጃቢነት ተመልሶ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ መድረክ ሲወጣ ቴዲን ባለቤቱ እጁን ይዛ ወደ ቤቱ…
በነገራችን ላይ ውዝግቡ የተጀመረው ቀደም ብሎ እንደሆነ ሲነገር ነበር፡፡ መቼ? መቼ መሰለህ? የጃኪ ጎሲንም ሆነ የቴዎድሮስ ታደሰን ዘፈኖች የሚያጅቡት ዛየን ባንዶች እንደሆኑ ከሳምንታት በፊት በተለቀቀው ማስታወቂያ ላይ ተገልጧል፡፡ ለኮንሰርቱ ተብሎ በታተመው ፖስተር ላይም አይተህ ከሆነ አጃቢው ባንድ ዛየን ባንድ ብቻ ነው፡፡
እናስ? እናማ ኮንሰርቱ ሊካሄድ ሁለት ቀን ሲቀረው ቴዲ በነአበጋዙ ሚሊኒየም ባንድ ነው የምዘፍነው አለ አሉ፡፡ በዚህ ሳቢያ ኮንሰርቱ እንዳይበላሽ በሚል የቴዲን ዘፈኖች ሚሊኒየም ባንዶች እንዲጫወቱለት ተደረገ፡፡ በዚህ ሳቢያ ቴዲ ወደ መድረክ አልወጣም ብሎ ወደ ቤቱ ሄዶ ስለነበር ከጃኪ በኋላ ስሙ ሲጠራ ያልነበረው እሱ ብቻ አልነበረም፤ ሚሊኒየም ባንድም አልነበረም… በል ቻዎ…
ቁምነገር መጽሔት በአዲስ አበባ የሚታተመው እንደዘገበው።

Wednesday, September 24, 2014

በቂሊንጦ ግንቦት 7 ነው ተብሎ የታሰረው ወጣት 10 ጥፍሮቹን ነቅለው ብልቱ ላይ የላስቲክ ውሃ አንጠልጥለው እንዳሰቃዩት ተጋለጠ



(ዘ-ሐበሻ) የግንቦት 7 አባል ነው ተብሎ የታሰረው አበበ ካሴ የተባለ ወጣት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በሕወሓት/ኢሕአዴግ ካድሬ ወታደሮች ከፍተኛ የሆነ ግፍ እየተፈጸመበት መሆኑን ከስፍራው ለዘ-ሐበሻ መረጃ ያደረሱ ወገኖች አስታወቁ።

“ከወደ ቂሊንጦ የደረሰኝ መረጃ እጅግ የሚዘገንና እንቅልፍ የሚነሳ ነው” በሚል መረጃውን ያቀበለን ውስጥ አዋቂ አበበ ካሴ ግንቦት 7 ነው በሚል የታሰረ ሲሆን መቀጣጫ እናደርግሃለን፤ ምስጢር አውጣ እያሉ በሚዘገንን መልኩ የ10 ጣቶቹን ጥፍሮች እንደነቃቀሉት አስታውቋል። እንደ መረጃ ምንጩ ገለጻ ከሆነ ብልቱ ላይ የታሸገ የላስቲክ ውሃ (ሃይላንድ) በማንጠልጠል ሲያሰቃዩት የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከብልቱ ፈሳሽ መውጣት መጀምሩም ተገልጿል። እንደመረጃ ምንጩ ገለጻ ከሆነ አበበ በብልቱ ላይ በደረሰበት ከፍተኛ ሕመም ህክምና እንዲደረግለት ቢጠይቅም “ሕክምና ማግኘት አይደለም ገና እንግድልሃለን” ብለው ከልክለውታል።
አበበ በአሁኑ ወቅት የእስረኛ መለያ መታወቂያውን መቀማቱን ያጋለጠው የመረጃ ምንጫችን የሚፈጸምበት ግፍ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መምጣቱን እና እየተፈጸመበት ያለው የጭካኔ ተግባርም በምን ዓይነት ቋንቋ መግለጽ እንሚቻል ከባድ እንደሆነ ገልጾልናል።

Sunday, September 21, 2014

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ለብድር ዕዳ አደጋዎች የመጋለጥ ዕድሏ እየሰፋ ነው አለ

ሰሞኑን ለሦስት ቀናት ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የኦፕሬሽን ዋና ኃላፊ ስሪ ሙሊያኒ ኢንድራዋቲ፣ እያደገ የመጣው የብድር ዕዳ መጠን በኢትዮጵያ ላይ አደጋዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ገለጹ፡፡ 
ኢንድራዋቲ ባለፈው ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ምንም እንኳን የአገሪቱ የብድር ዕዳ መጠን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም፣ የዕዳውን መጠን በግልጽነት ለማስተዳደር የሚችልና ግልጽነት የሰፈነበት አስተዳደር ማስፈን የመንግሥት ግዴታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አገሪቱ ያለባት ጠቅላላ የብድር መጠን 20 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 12 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ምንጮች የተገኙ ብድሮችን የሚሸፍን የዕዳ መጠን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት አኳያ የዕዳው ድርሻ 44 ከመቶ መድረሱን ይጠቁማል፡፡ 
ኢንድራዋቲ እንደሚገልጹት፣ ይህ አኃዝ ዝቅተኛ በሚባለው የዕዳ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት የኢንቨስትመንት ወጪዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ምክንያት የዕዳ መጠኑን በዚያው ልክ እያደገ በመሆኑ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በሚመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከሚመለከታቸው ሚኒስትሮች ጋር መነጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡ ከውይይቶቹ መካከልም በመንግሥት አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርሞች ላይ ያተኮረው አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህም መንግሥት በአስተዳደራዊ መዋቅሮቹ ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ ግልጽነትና ኢኮኖሚውን በብቃት የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ 
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን  የኢንቨስትመንት ወጪን መነሻ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ እየጨመረ የሚገኘውን የብድር ዕዳ መጠንና ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል አሠራር ማምጣት እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡ 
‹‹ይህንን ለማከናወን አስተማማኝ የፋናይናንስ ሪፖርት ያስፈልጋል፡፡ ግልጽነትና ወጥነት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ተዓማኒነት ያለው መረጃ መኖሩ ግድ ይላል፡፡ አሁን እየታየ ያለው የብድር ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ የተጋላጭነት አደጋ ማስከተሉ በእርግጠኝነት የማይቀር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የብድር ዕዳዋን ለማቃለል የወጪ ንግድ ሚዛኗ ወሳኝ መሆኑን ኢንድራዋቲ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ባለፉት ሦስት ዓመታት በወጪ ንግድ መስክ አገሪቱ ዝቅተኛ ውጤት ስታዝመገዘብ መቆየቷ ለብድር ዕዳ ያላትን ተጋላጭነት አስፍቶታል ይባላል፡፡ 
አገሪቱ ስታዝመግብ የቆየችው የኢኮኖሚ ዕድገት መልካም የሚባል መሆኑን የጠቀሱት ኢንድራዋቲ፣ ይህም ሆኖ ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ብዙ እንደሚቀረው ገልጸዋል፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት በርካታ የሥራ መስኮችን ሊፈጥሩ የሚችሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማምጣት ብዙ መንገድ ይቀረዋል ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ፣ ባንኩ የኢንዲስትሪ ዞኖች ግንባታን ፋይናንስ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውሰዋል፡፡ በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ሁለተኛ ምዕራፍና በአቃቂ ቃሊቲ ቂልንጦ አካባቢ ለሚገነቡ ሁለት የኢንዱስትሪ ዞኖች የሚውል የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር መፍቀዱን፣ በኢትዮጵያ የባንኩ ዳይሬክተር ጉዋንግ ዚ ቼን ገልጸዋል፡፡ 
ባንኩ ለመሠረተ ልማት ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ለመሠረታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ተዘዋውረው በጎበኟቸው የሴፍቲኔት ጣቢያዎች ጥሩ ውጤት እንዳዩ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ተናግረው፣ እየጨመረ በመጣው የከተሞች የምግብ እጥረት ተጋላጭነት ሳቢያ በድምሩ አሥር ሚሊዮን ሰዎች በሴፍቲኔት ፕሮግራም ይታቀፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ይፋ አድርገዋል፡፡ 
ስሪ ሙልያኒ ኢንድራዋቲ የዓለም ባንክን ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ የኢንዶኔዥያ የፋይናንስ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢኮኖሚ ጉዳዮች አስተባባሪ ሚኒስትር በመሆንም ሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 የዓለም ባንክን የተቀላቀሉት ኢንድራዋቲ፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ደረጃ የሚመሯቸው በርካታ መስኮች አሉ፡፡ በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ሥልጣናቸው የባንኩን የአካባቢያዊ ሥራዎች በጠቅላላ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሪፖርተር ዘግቧል 

Tuesday, September 16, 2014

በአይሳኢታ፣ በዱብቲ፣ በአዋሽ፣ በአሚ ባራ፣ በገዋኔ፣ በአፍዴራ፣ በዶቢና ሚሌ የሚገኙ አፋሮች መሬታቸውን ተቀምተው በርሃብ እየተቆሉ ነው ።

አኩ ኢብን ከአፋር ለዘሐበሻ እንደዘገበው
የደርግ ስርዓት ወድቆ የኢህአዴግ መንግስት ሲመጣ ብዙ የአፋር መሬት ወደ ትግራይ ክልል እንዲመለስ ተደርጓል። በሰሜናዊው የአፋር ክልል በዳሉል ወረዳ ይተዳደሩ የነበሩ ብዙ የአፋር ህዝቦች በግዴታ በትግራይ ክልል ውስጥ እንዲተዳደሩ ተደርገዋል!
ለምሳሌ፦ ያህል፥ ታላክ፣ ጎደለ፣ ሰሄሎ እና ሰውነ ሲሆን ከዚህ በላይ ስማቸው በተጠቀሱት ቦታዎች ከኢህአዴግ ሰርዓት በፊት ከአጼዎች ዘመን ጀምሮ የአፋር መሬት እንደነበረ ይታወቃል። ታላክ እና ጎደለ እሰከ ሰሄሎ በደጅ አዝማች አህመድ ሲተዳደሩ ሰውነ ደግሞ በኦና ማሕሙድ ይተዳደር ነበር።
afar 1
afar 2
በዚህ አካባቢ የሚተዳደሩ የአፋር ህዝቦች እስካሁን ድረስ በቋንቋቸው የመማር ማስተማር እንዲሁም ባህላቸውን የማሳደግ የሰብዓዊ መብት ያላገኙ ሲሆን በሚኖሩበት የትግራይ ክልል እንኳን የአፋር ብሄረሰብ አይባሉም ኢህአዴግ ይኸው ቆምኩላችሁ መብታችሁን አስከበርኩላችሁ እያለ የአፋር ህዝብ ግን ገና ጭቆና ላይ መሆኑን ለመላው የኢትዮጵያ ወገኖቻችንና ለዴሞክራሲም ሆነ ለሰብዓዊ መብት የሚታገሉ የመብት ታጋዬች ሊያውቁልን ይገባል! ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ደርግን ለመዋጋት ወደ ጫካ ሲገቡ ይሄ የአፋር ህዝብ ለትግራይ ህዝብ የቅርብ ጎረቤት ስለነበር ምግባቸውን አብስለው ለተጋዬች ከማቅረብ ጀምሮ ከጎናቸው የቆመ ህዝብ ቢሆንም ዛሬም ከጭቆና ልወጡ አልቻሉም።

ወድ የተከበረችሁ ወገኖቼ ሆይ ይሄን ስናገር ግን የቀረው የአፋር ህዝብ መብት ተክሮለታል ማለት አይደለም! በክልላችን በወያኔ ያልተወረረ የአፋር መሬት የለም። በአይሳኢታ፣ በዱብቲ፣ በአዋሽ ፣በአሚ ባራ፣ በገዋኔ ፣በአፍዴራ ፣በዶቢና ሚሌ የሚገኙ አፋሮች በአሁኑ ጊዜ ከመሬታቸው ተፈናቅለው በረሀብ እየተሰቃዩም ይገኛሉ።

የተንዳሆ የስኳር ፋብሪካ የተጀመረው በ2001 ዓ.ም ቢሆንም እሰከ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ከስኳር ችግር አልወጣም። ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠሩት የህወሃት ባለ ስልጣናት ሲሆኑ አብዛኛቸው ከመከላኪያ ሰራዊት በጡረታ የወጡ መኮነኖች ናቸው! የአፋር ክልል መንግስትም ቢሆን ለስራቸው የሚሰጠውን ባጀት ወደ ውጭ ሀገር እየላኩ ማስቀመጥ ብቻ ነው!! ሌላው ቀርቶ በአፋር ክልል በሰላም ሲኖሩ የነበሩ የአማራና የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን በግዳጅ ከአፋር ክልል እያስወጡ ይገኛሉ። 

በዚህ አመት ብቻ ከ400 ሺ በላይ የትግራይ ተወላጆች በሰፈራ ፕሮግራም ወደ አፋር ክልል ገብተዋል!!
በመጨረሻም:- የአፋር ህዝብ ከኢትዮጵያ ነፃነት ታጋዮች ጋር ለሚደረገው ትግል ከዳር እስከ ዳር ዝግጁ መሆኑን በአፋር ወጣቶች ስም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። የአፋር ህዝብ ይህ የአንባገነን ስርዓት አብቅቶ የነፃነት ፀሃይ የምትወጣበት ቀን በጉጉት የሚጠብቅ ጭቁን ህዝብ ነው!
ነፃነት ለኢትዮጵያ

Thursday, September 4, 2014

አንጀሊና ጆሊ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰራችው ”ድፍረት” ፊልም በፖሊሶች ድፈረት በርካታ ”ትላልቅ” እንግዶች በተገኙበት ሊመረቅ ሲል ታገደ፤ አርቲስቶች አዝነዋል እኛም የጥንቸሏን ተረት አስታውሰናል…


 አንጀሊና ጆሊ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰራችው ”ድፍረት” ፊልም በፖሊሶች ድፈረት በርካታ ”ትላልቅ” እንግዶች በተገኙበት ሊመረቅ ሲል ታገደ፤ አርቲስቶች አዝነዋል እኛም የጥንቸሏን ተረት አስታውሰናል…
ሜሮን ጌትነት በመሪ ተዋናይነት ሰርታበታለች የተባለው ይህ ፊልም የታገደው በፖሊሶች ቀጭን ትዛዝ ነው። በርካታ አርቲስቶች የዚህ አይነት ነገር ሲያጋጥማቸው ለመጀመሪያ ግዜ መሆኑን ተናግረዋል።
 እኛ ግን የነጻ ጋዜጠኞች ማህበር ስብሰባ ፖሊስ በትኑ ሲል ሰምተን እናውቃልን እና፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሰብሰባዎች ከተሰበሰቡ በኋላ ብዙ ጊዜ አምቦውሃው መንግስታችን ሲበትነው አየተናልና፣ የባለራዕይ ወጣቶችን ሰላማዊ ስብሰባ በተደጋጋሚ ያለምንም ሀጋዊ ከለላ ሲያገደው አየተናልና… የዳዊት ጸጋዬ ቲያትር ማስመረቂያ አጥቶ ከሰማያዊ ፓርቲዎች ጋር ቦታ ፍለጋ ሲነከራተት መሰንበቱን እናውቃለነና ኧረ ስንቱ…
(በነገራችን ላይ ዘ ዲክታተር የተባለው አስቂኝ ፊልም እንኳ፤ ባንድ ወቅት ርሳቸው ሬሳ ከመሆናቸው በፊት…(ውይ እኔ ደግሞ አንዳንዴ አበዛዋለሁ አቶ መለስ ”ከመሰዋታቸው” በፊት ማለቴ ነው… እና ያኔ ታግዶ ነበር።) ይሄንን ሁሉ ያልሰሙ አርቲስቶች ዛሬ ተደነቁ እንጂ መንግስታችን ማገድ ብርቁ አይደለም።
የጥንቸሏ ተረት ምን መሰላችሁ…
ዝሆን እና ጥንቸል ሲኒማ ቤት ተገናኙ አሉ፤ ከዛ ዝሆን ሆዬ ከጥንቸል ፊት ሄዱ ቁጭ ብሎ ከለላት አይገልጸውም…(ከፊልም ቤት አስወጣት ብንል ይሻላል…ሃሃ) እና ታድያ ጥንⶨሊት ዝሆንን በቡጢ እየደበደበች በሹክሹክታ ”እረ በናትህ ዝሆን አይደብርህም እንዴ ከለልከኝ እኮ…” እያለች ብትወተውት ብትወተውት አለሰማ አላት… (ዝሆን እኮ ጆሮው ትልቅ ነው እንጂ በተልቁ አይሰማም… ) ከዛ ብዚህ የተበሳጨችው ጥንቸል ከፊት ለፊቱ ሄዳ ቁጭ አለች እና ፊልሟን ኮመኮመች በማብቂያው ላይ ዞር ብላ ”አየህ አይደል የመከለል ነገር እንዴት እንደሚያበሳጭ” አለችው አሉ…
አርቲስቶቻችን የመታገን ነገር አያችሁት አየደል እንዴት እንደሚያበሳጭ… በፊልም እና ድራማ ስራ ተወጥራችሁ ልብ አላላችሁትም እንጂ እናንተ ላይ ሀዝቡ ላይ የደረሰው እገታ ዝሆኑ ጥንቸሏን ሲከልላት የነበረው አይነት ነው…!
ይሄንን እና ሌሎች እገታዎችን ለመቃወም እና መጪው አመት ብሩህ እንዲሆን ለመስበክ ነው #Blackweek ብለን እየዘከርን ያለነው፤
ለማንኛውም እንሆ ፊልሙ በፖሊስ ቀጭን ትዛዝ ሲታገድ የሚያሳይ ቪዲዮ!

ሐሰን ሺፋ ከፌደራል ፖሊስ ም/ኮሚሽነርነት ሥልጣናቸው ተነሱ

(ዘ-ሐበሻ) የሕወሓት ነባር ታጋዮች መካከል አንዱ የነበሩትና ሕወሓት በተከፋፈለበት ወቅት የነስዬ አብርሃ ወገንን ተቀላቅለው በኋላም ወደ አቶ መለስ ወገን ይቅርታ ጠይቀው የተመለሱት የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሐሰን ሺፋ ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉ አነጋጋሪ መሆኑን ለዘ-ሐበሻ የደረሱ መረጃዎች አመለከቱ።

hasen shifa
የፌዴራል ፖሊስ የዘ-ሐበሻ ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት አቶ ሐሰን ሽፋ በተለይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ እንቅስቃሴን የሕወሓት መንግስት እንዳሰበው በተንኮል ሊቆጣጠረው ካለመቻሉና በስርዓቱ ባለስልጣናት ውስጥ በተነሳው ያለመተማመን ችግር ጋር ተያይዞ ካሉበት ቦታ እንዲነሱ ተደርገዋል።
አቶ ሐሰን በምክትል ኮምሽነርነት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩን ከታች ሆነው ሲዘውሩ የቆዩ ሲሆን በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በትግራይ፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብና በሌሎችም ስፍራዎች ሥርዓቱ ለፈጸማቸው ጭፍጨፋዎች ተጠያቄ እንደሆኑ የሚናገሩት የዘ-ሐበሻ ምንጮች በድንገት ከዚህ ስልጣናቸው ተነስተው ወደ ፌደራል ጉዳዮች ሚ/ር መስሪያ ቤት ውስጥ እንዲሰሩ መላካቸው የስርዓቱን ደጋፊዎች ሳይቀር “ድርጅቱ በውስጡ ምን እየሆነ ነው?” በሚል እያነጋገረ ነው ብለዋል።
በሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ስር ያሉ ባለስልጣናት እርስበእርሳቸው አለመሰማማታቸው እንዲህ ያሉ ከስልጣን መነሳቶችና/ መዘዋወሮች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።