Friday, September 26, 2014

የቴዎድሮስ ታደሰ እና የጃኪ ጎሲ ፍጥጫ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ መድረክ ጀርባ፤ ጃኪ ቴዎድሮስ ታደሰን ለምን ማጣጣል አስፈለገው?

ስለ ጃኪ ጎሲ ኮንሰርት ውዝግብ
ይህ የቁም ነገር መፅሔት ቅ ፅ 13 ቁጥር 187 ወሬ ልንገርህ ዕምድ ነው
መቼም አንድም አልበም ሳያወጣ በነጠላ ዜማዎቹ ብቻ የሚሊዮኖችን የሙዚቃ አፍቃሪያንን ልብ ስለተቆጣጠረው ጃኪ ጎሲ አላውቅም አትለኝም! ጃኪ ጎሲ ማነው? በእርግጥ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ጃኪ ጆሲ አይደለም፡፡ የመዝገብ ስሙ ጎሳዬ ቀለሙ ነው፡፡ ራሱ ነው ስሙን አሳጥሮ ጃኪ ጎሲ ያለው፡፡
እናስ? እናማ ባለፈው ሳምንት ለአዲሱ 2007 መግቢያ በከተማችን ከተዘጋጁት የሙዚቃ ኮንሰርቶች መካከል አንዱ የዚህ ወጣት ድምፃዊ ጃኪ ጎሲ ነበር፡፡ ታዲያልህ ለዚህ ዘመነኛ ወጣት ገና አንድ አልበም ሳያወጣ የተከፈለው ክፍያ ስንት እንደሆነ ሰምተሃል?ማን ነግሮኝ? በል ከተማው ውስጥ የለህም ማለት ነው፡፡ ለማንኛውም ለዚህ የመጀመሪያ ኮንሰርቱ 1.5 ሚሊዮን ብር እንደተከፈለው ይነገራል፡፡ ያው ክፍያው ቫትን ያካት አያካት ግልፅ አይደለም፡፡


እናስ? ጳግሜ 5 ምሽት በሚሊኒየም አዳራሽ ኮንሰርቱን ለማሳየት ቀጠሮ የተያዘለት ጃኪ ጎሲ ብቻ አልነበረም፡፡ ደግሞ ማን አለ አልክ? ሁለቱ አንጋፋ አርቲስቶችም ጃኪ ጎሲን እንዲያሯሩጡ ተጋብዘው ነበር፡፡ ማንና ማን መሰሉህ? አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴና ሌላው አንጋፋ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ ነበሩ፡፡
በፕሮግራሙ ቅደም ተከተል መሰረት አለማየሁ እሸቴ መጀመሪያ ገብቶ ከዘፈነ በኋላ ቴዎድሮስ፤ ከዚያ ጃኪ ጎሲና ቴዲ እየተፈራረቁ እንዲዘፍኑ ነበር እቅዱ፡፡ እናስ? እናማ በፕሮግራሙ መሠረት አለማየሁ ከአራት በላይ ዘፈኖቹን /ተማር ልጄን ጨምሮ/ ከተጫወተ በኋላ በዛው ዕለትና ሰዓት በካፒታል ሆቴል ሌላ መድረክ ስለነበረው ሹልክ ብሎ አመለጠ፡፡
ከዚያስ? ከዚያማ ያው ቴዎድሮስና ጃኪ መድረኩን በየተራ በመውጣት ተመልካቹን ካዝናኑ በኋላ የተመስገን ልጆች መድረኩን ተረከቡ፡፡ የተሜ ልጆች ለሁለት ዘፈን መድረክ ላይ ወጥተው አርባ አምስት ደቂቃ ሲቆዩ ሰዓቱ ወደ ስምንት ሰዓት ተኩል ደርሶ ነበር፡፡ በዚህ መሀል ውዝግብ ተጀመረ፡፡ በማንና በማን? በጃኪና በቴዎድሮስ ታደሰ ማናጀሮች መካከል፡፡ ለምን መሰለህ? የተመስገን ልጆች ከመድረክ ሲወርዱ መጀመሪያ መውጣት ያለብኝ ‹እኔ ነኝ – እኔ ነኝ› በሚል ማለት ነው፡፡
ለምን መሰለህ? የኮንሰርቱ ማብቂያ ሰዓት እየተጠናቀቀ ስለነበር ጃኪ ከወጣ በኋላ ከመድረክ ሲወርድ ተመልካቹ ወደ ቤቱ ስለሚሄድ መጀመሪያ መውጣት ያለብኝ እኔ ነኝ ያለው ቴዲ ነበር አሉ፡፡ በዚህ የመድረክ ጀርባ ውዝግብ ሲካሄድ የተመስገን ልጆች ውዝዋዜያቸውን ጨርሰው ወደ መድረክ ጀርባ ተመልሰው ነበር፡፡ ውዝግቡ በሁለቱ አርቲስቶች ማናጀሮች መካከል ለተወሰነ ደቂቃ ከተካሄደ በኋላ የቴዎድሮስ ታደሰ ማናጀር ባለቤቱ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰች፡፡
ውሳኔው ምን ቢሆን ጥሩ ነው? መጀመሪያ ጃኪ ጎሲ እንዲዘፍን ከተደረገ ቴዲ ከእሱ በኋላ አይዘፍንም አለች፡፡ እናስ? እናማ ጃኪ ጎሲ በዛየን ባንድ አጃቢነት ተመልሶ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ መድረክ ሲወጣ ቴዲን ባለቤቱ እጁን ይዛ ወደ ቤቱ…
በነገራችን ላይ ውዝግቡ የተጀመረው ቀደም ብሎ እንደሆነ ሲነገር ነበር፡፡ መቼ? መቼ መሰለህ? የጃኪ ጎሲንም ሆነ የቴዎድሮስ ታደሰን ዘፈኖች የሚያጅቡት ዛየን ባንዶች እንደሆኑ ከሳምንታት በፊት በተለቀቀው ማስታወቂያ ላይ ተገልጧል፡፡ ለኮንሰርቱ ተብሎ በታተመው ፖስተር ላይም አይተህ ከሆነ አጃቢው ባንድ ዛየን ባንድ ብቻ ነው፡፡
እናስ? እናማ ኮንሰርቱ ሊካሄድ ሁለት ቀን ሲቀረው ቴዲ በነአበጋዙ ሚሊኒየም ባንድ ነው የምዘፍነው አለ አሉ፡፡ በዚህ ሳቢያ ኮንሰርቱ እንዳይበላሽ በሚል የቴዲን ዘፈኖች ሚሊኒየም ባንዶች እንዲጫወቱለት ተደረገ፡፡ በዚህ ሳቢያ ቴዲ ወደ መድረክ አልወጣም ብሎ ወደ ቤቱ ሄዶ ስለነበር ከጃኪ በኋላ ስሙ ሲጠራ ያልነበረው እሱ ብቻ አልነበረም፤ ሚሊኒየም ባንድም አልነበረም… በል ቻዎ…
ቁምነገር መጽሔት በአዲስ አበባ የሚታተመው እንደዘገበው።

No comments:

Post a Comment