ሰሞኑን ለሦስት ቀናት ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የኦፕሬሽን ዋና ኃላፊ ስሪ ሙሊያኒ ኢንድራዋቲ፣ እያደገ የመጣው የብድር ዕዳ መጠን በኢትዮጵያ ላይ አደጋዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ገለጹ፡፡
ኢንድራዋቲ ባለፈው ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ምንም እንኳን የአገሪቱ የብድር ዕዳ መጠን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም፣ የዕዳውን መጠን በግልጽነት ለማስተዳደር የሚችልና ግልጽነት የሰፈነበት አስተዳደር ማስፈን የመንግሥት ግዴታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አገሪቱ ያለባት ጠቅላላ የብድር መጠን 20 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 12 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ምንጮች የተገኙ ብድሮችን የሚሸፍን የዕዳ መጠን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት አኳያ የዕዳው ድርሻ 44 ከመቶ መድረሱን ይጠቁማል፡፡
ኢንድራዋቲ እንደሚገልጹት፣ ይህ አኃዝ ዝቅተኛ በሚባለው የዕዳ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት የኢንቨስትመንት ወጪዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ምክንያት የዕዳ መጠኑን በዚያው ልክ እያደገ በመሆኑ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በሚመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከሚመለከታቸው ሚኒስትሮች ጋር መነጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡ ከውይይቶቹ መካከልም በመንግሥት አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርሞች ላይ ያተኮረው አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህም መንግሥት በአስተዳደራዊ መዋቅሮቹ ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ ግልጽነትና ኢኮኖሚውን በብቃት የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመንት ወጪን መነሻ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ እየጨመረ የሚገኘውን የብድር ዕዳ መጠንና ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል አሠራር ማምጣት እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡
‹‹ይህንን ለማከናወን አስተማማኝ የፋናይናንስ ሪፖርት ያስፈልጋል፡፡ ግልጽነትና ወጥነት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ተዓማኒነት ያለው መረጃ መኖሩ ግድ ይላል፡፡ አሁን እየታየ ያለው የብድር ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ የተጋላጭነት አደጋ ማስከተሉ በእርግጠኝነት የማይቀር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የብድር ዕዳዋን ለማቃለል የወጪ ንግድ ሚዛኗ ወሳኝ መሆኑን ኢንድራዋቲ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ባለፉት ሦስት ዓመታት በወጪ ንግድ መስክ አገሪቱ ዝቅተኛ ውጤት ስታዝመገዘብ መቆየቷ ለብድር ዕዳ ያላትን ተጋላጭነት አስፍቶታል ይባላል፡፡
አገሪቱ ስታዝመግብ የቆየችው የኢኮኖሚ ዕድገት መልካም የሚባል መሆኑን የጠቀሱት ኢንድራዋቲ፣ ይህም ሆኖ ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ብዙ እንደሚቀረው ገልጸዋል፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት በርካታ የሥራ መስኮችን ሊፈጥሩ የሚችሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማምጣት ብዙ መንገድ ይቀረዋል ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ፣ ባንኩ የኢንዲስትሪ ዞኖች ግንባታን ፋይናንስ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውሰዋል፡፡ በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ሁለተኛ ምዕራፍና በአቃቂ ቃሊቲ ቂልንጦ አካባቢ ለሚገነቡ ሁለት የኢንዱስትሪ ዞኖች የሚውል የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር መፍቀዱን፣ በኢትዮጵያ የባንኩ ዳይሬክተር ጉዋንግ ዚ ቼን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ለመሠረተ ልማት ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ለመሠረታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ተዘዋውረው በጎበኟቸው የሴፍቲኔት ጣቢያዎች ጥሩ ውጤት እንዳዩ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ተናግረው፣ እየጨመረ በመጣው የከተሞች የምግብ እጥረት ተጋላጭነት ሳቢያ በድምሩ አሥር ሚሊዮን ሰዎች በሴፍቲኔት ፕሮግራም ይታቀፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ይፋ አድርገዋል፡፡
ስሪ ሙልያኒ ኢንድራዋቲ የዓለም ባንክን ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ የኢንዶኔዥያ የፋይናንስ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢኮኖሚ ጉዳዮች አስተባባሪ ሚኒስትር በመሆንም ሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 የዓለም ባንክን የተቀላቀሉት ኢንድራዋቲ፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ደረጃ የሚመሯቸው በርካታ መስኮች አሉ፡፡ በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ሥልጣናቸው የባንኩን የአካባቢያዊ ሥራዎች በጠቅላላ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሪፖርተር ዘግቧል
ሪፖርተር ዘግቧል
No comments:
Post a Comment