Tuesday, January 21, 2014

ለጨጓራ መላጥ (አልሰር) በሽታ መፍትሄው ምንድን ነው

Health

ዘ-ሐበሻዎች በጋዜጣችሁ እንዲሁም በድረገጻችሁ የምታቀርቧቸው ጤና ነክ ዘገባዎች በጣም በፍቅር ነው የማነባቸው። ዛሬ ወደ እናንተ እንድጽፍ ያስገደደኝ አንድ ጉዳይ ገጥሞኛል። ‹ለጨጓራ መላጥ /አልሰር/ በሽታ መፍትሄው ምንድን ነው? ምላሻችሁን እጠብቃለሁ።

ሰለሞን
የዶ/ር ዓብይ ዓይናለም ምላሽ፦ ሰለሞን በቅድሚያ ለላክልን ደብዳቤ በጣም እናመሰግናለን፡፡ ወደ ጥያቄህ ስንመለስ ከሶስት ወር በፊት አንድ ክሊኒክ ሄደህ የጨጓራ መላጥ /አልሰር/ መታመምህ እንደተነገረህ ገልፀኻል፡፡ የመድሃኒቱን ስም ባትጠቅሰውም በሐኪም የታዘዘ መድሃኒት ተጠቅመህ ምንም አይነት መፍትሄ እንዳላገኘህ ተረድተናል፡፡


አንባቢያችን እንደገለፅከው የሆድ ውስጥ መቃጠል፣ ማቅለሽለሽና ትውከትን የመሳሰሉ ህመም ነክ ምልክቶች ተስተውለዋል፡፡ በእርግጥ አንተ የገለፅካቸውን ጨምሮ የሆድ መነፋት፣ በትንሽ ምግብ የሆድ መሙላት ስሜት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ደም የተቀላቀለበት ትውከት፣ የአይነምድር መጥቆርና ደም የቀላቀለ አይነምድር መውጣት ለጨጓራ መላጥ /አልሰር/ በሽታ መኖር ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ህመም ነክ ምልክቶች ለጨጓራ መላጥ በሽታ ብቻ ምልክት ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ቀለል ባለ የጨጓራ መታወክ ለሐሞት ቀረጢት ችግሮችና ለሌሎች መሰል በሽታዎች መከሰትም ጠቋሚ ምልክት ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል፡፡ ለጨጓራ መላጥ በሽታ የሚጋለጡ የተለያዩ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለአብነት ሄሊኮባክተር ፓይሎሪ የሚባል ባክቴሪያ በሚያመጣው ኢንፌክሽን የተነሳ የአሲድ ምርት መዛባትና የግድግዳው ስስ ሽፋንን በማሳጣት ለቁስለት ያጋልጠዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለስቃይ ማስታገሻ ተብለው በሐኪም የሚታዘዙ እንደ አስፕሪን የመሰሉ መድሃኒቶች የጨጓራ ቁስለትን የሚያስከትሉ ሲሆን በዘር፣ በሲጋራ በማጨስና አልኮል በመጠጣት ለጨጓራ መላጥ /አልሰር/ ችግር የመጋለጥ እድል ይኖራል፡፡

የባህር ዳሩ ሰለሞን የአንተ ጤና ችግር በትክክል የጨጓራ መላጥ /አልሰር/ መሆኑን በትንፋሽ፣ በደምና በሰገራ የሄሊኮባክተር ፓይሎሪ ምርመራን በማካሄድ በተጨማሪም የኢንዶስኮፒ ምርመራ አድርገህ የህመምህን ምንነት ለማረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት ብትሰጥ ጠቃሚ ነው ብለን እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም የችግሩ ምንነት በግልፅ ካልታወቀ ትክክለኛና ውጤታማ መፍትሄ ለመስጠት አዳጋች ነው የሚያደርገው፡፡ ውድ የባህርዳሩ አንባቢያችን የጨጓራ መላጥ /አልሰር/ ችግር በወቅቱ ታክሞ መዳን ካልተቻለና ከዘገየ የመድማት፣ የጨጓራ ግድግዳ መበሳትና የአንጀት መጥበብ በተጨማሪም ምግብ ያለማሳለፍ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

በግልፅ መገንዘብ እንደሚቻለው የጨጓራ መላጥ /አልሰር/ ማለት በጨጓራ የውስጠኛው ግድግዳ ሽፋን ላይ የሚፈጥረው መላጥ ሲሆን አብዛኛው ጊዜ የመላጥ ችግር የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የጨጓራ ግድግዳና የመጀመሪያው ትንሹ አንጀት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ የጨጓራ መላጥ በሽታ ሁለት አይነት ነው፡፡ የመጀመሪያው ጋስትሪክ አልሰር ሲሆን ሁለተናው ዲዎድናል አልሰር በመባል ይታወቃል፡፡ አንባቢያችን ሰለሞን ይህ በሽታ አንተን ጨምሮ በዓለም ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠቃል፡፡ በሀገራችንም በጥልቀት የተጠኑ ጥናቶች ባይኖሩም በጤና ተቋማት የተገኙ መረጃዎችን መሰረት አድርገው የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በሀገራችን የችግሩ ስፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱን እያሰፋ መሄዱን ነው የሚያረጋግጡት፡፡ በሽታው ሳይባባስና ስር ወደ ሰደደ ችግርነት ሳይለወጥ በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ከተደረገ ሙሉ በሙሉ መዳን የሚችል ነው፡፡ የጨጓራ በሽታ ህክምና እንደ መንስኤውና እንዳስከተለው የጉዳት አይነት ይለያያል፡፡ ጠቅለል ተብለው ሲታይ የህክምና መፍትሄዎች /የህክምና ዘዴዎች/ የሚከተሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

- ኤች.ፓይሎሪን የማጥፋት ህክምና ይካሄዳል
- የአሲድ መቀነሻ መድሃኒቶች ይሰጣሉ
- የጨጓራ መላጥ ህመምን ያስከተሉት ሌሎች ህመሞች ተብለው የተወሰዱ መድሃኒቶች ከሆኑ እነዚህን በማስቆም ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
- ሲጋራ ማጨስን አልኮል መጠጣት ማቆም
- የህመሙን ስሜት የሚቀሰቅሱ ምግቦችን አለመመገብ
- በህመሙ ሳቢያ የተከሰቱ ጉዳዮችን በአግባቡ ማከም ከተቻለ የጨጓራ አልሰርን/መላጥን በተገቢው መንገድ አክሞ ማዳን ይቻላል፡፡
ጠያቂያችን ሰለሞን መድሃኒት ተጠቅመህ እንዳልተሻለህ መግለፅህ ይታወሳል፡፡ በእኛ እምነት ከሁሉም አስቀድመህ የተሻለ ህክምና ወደ ሚሰጥበት የጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ብታደርግና የበሽታውን ትክክለኛነትና መንስኤውን ብታረጋግጥ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በተማሪም በሐኪም የሚታዘዝልህን መድሃኒቶች በተገቢው ጊዜና መጠን መጠቀም መቻልህን መዘንጋት የለብህም፡፡ ከዚህ በተረፈ ለጤና ችግሩ መባባስ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች ራስህን በማራቅ ከችግሩ ሙሉ በሙሉ መላቀቅ የምትችል መሆኑን እንመክርሃለን፡፡

No comments:

Post a Comment