የኢትዮጵያ መንግስት ኢቦላን ለምን ፈለገው…!?
የኢትዮጵያ መንግስት ኢቦላን ለምን ፈለገው…!
ትላንት እነ ዮሃንስ ሞላ (ዮሃንስ ሞላ የብርሃን ልክፍት መድብል አሰናጅ ነው) እነርሱ የሚቀኙላትን ቅዳሜን የመሰለች ቀን ራሴን ክፉኛ ታምሜ አሳለፍኳት። ከመዕራብ አፍሪካ የመጣ ሰው ጋር ባለመገናኘቴ እንጂ የትኩሳቴ ነገር በሌላ የሚያስጠረጥር ነበር። (ሌላ የተባለው ኢቦላ ነው… ደጋግሞ በመጥራት ራሱ ይመጣብን ይሆን እንዴ እያልን ተሳቀን ሞትን እኮ ጃል…!
ከትላንት በስቲያ አይደል እንዴ… አየር መንገዳችን ከዩንጋንዳ ካምፓላ የመጣ አንድ ሰውዬ የበዛ ትኩሳት ታይቶበታል ብሎ ለኢቦላ መመርመሪያ ጣቢያ በተዘጋጀ ልዩ ስርፋ አስገብቶ የበዛ ምርመራ ሲያደረግለት ያየነው…!
እኔ የምለው እንዲህ ምልክት የሚመስል ነገር ሲታይ አፋጣኝ ምርመራ ማድረጉ ባልከፋ… ነገር ግን አየር መንገዳችን እስካሁንም ድረስ በመጨባበጥ ሁላ የሚተላለፈው አደገኛ ቫይረስ ወደተቀሰቀሰብት ምዕራብ አፍሪካ በረራ ማድረጉ ምኑን ተማምኖ ነው.. እንደሆነ ለምን አይነገረንም…!
በርካታ ሀገሮች፤ ለዛው በህክምናውም በመከላከሉም ዋዛ ያልሆኑቱ፤ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ድርሽ አንልም ብለው ሲታቀቡ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርስ ምልስ፣ ድርስ ምልስ… እያለ እንደ ውሃ ቀጂ ሲመላልስ ብናይ የምርም ”የኢትዮጵያ መንግስት ኢቦላን ለምን ፈለገው…!” ብለን እየተጨነቅን እንገኛለን። መንግስት ኢቦላን አልፈለገውም ብሎ የሚሞግተን አካል ቢመጣ እንኳ ቢያንስ ነገር ሲፈልገው እያየን ነው ብለን እማኝነታችንን መስጠታችን አይቀሬ ነው…
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነገር ከገባ በቀላሉ አይወጣም። እንኳንስ ኢቦላ ይቀርና ኢህአዴግም እንኳ አልወጣ ብሎናል… (ልል ነበር ”ጽንፈኛ ዲያስፖራ ተቃዋሚ…” እንዳልባል ብዬ ትቼዋለሁ…) እውነቱን ለመናገር ግን አንድ መንግስት እንደ መንግስት ከሚያሳዩት ነገሮች አንዱ በህዝቡ ላይ ስጋት የሚሆኑ ነገሮች እንዳይከሰቱ መከላከል ነው። ሆን ብሎ በክፉ ልቦና ተነሳስቶ፤ አልያም ደግሞ በድንገት እና በነዋይ ፍቅር ተሳስቶ ህዝቡን ለስጋት የሚዳርግ ከሆነ መንግስት ሳይሆን መቅሰፍት ነው ብለን ከመደምደም ወደኋላ አንልም።
እናም አየር መንገዳችን፤ በበኩሌ ሳልናገር ብዬ እንዳይጸጽተኝ፤ ይሄ ኢቦላ የተባለ ክፉ ደዌ ወደ ሀገር ቤት ቢገባ ካንተ ራስ አንወርድም እና ካሁኑ ወደ አደገኛ ሀገሮች ከመብረር ክንፍህን ሰብስብ ለማለት እወዳለሁ!
ከአቤ ቶክቻው
No comments:
Post a Comment